የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 7

7
1ስለዚህም ንጉሡና ሃማን ለሁለተኛ ጊዜ ከአስቴር ጋር ለመጋበዝ አብረው ሄዱ፤ 2የወይን ጠጅ በመጠጣትም ላይ ሳሉ ንጉሡ “አስቴር ሆይ! ምን እንደምትፈልጊ ንገሪኝ፤ የፈለግሺውን ነገር ሁሉ እፈጽምልሻለሁ፤ የመንግሥቴን እኩሌታ እንኳ ቢሆን እሰጥሻለሁ” ሲል እንደገና ጠየቃት።
3አስቴርም “ንጉሥ ሆይ! በፊትዎ ሞገስ አግኝቼ ከሆነና በትሕትና የማቀርብልዎትን ጥያቄ ሊቀበሉኝ መልካም ፈቃድዎ ከሆነ፥ የእኔ ፍላጎት እኔም ሆንኩ ወገኖቼ በሕይወት መኖር እንድንችል ነው፤ 4እነሆ እኔና ወገኖቼ ለባርነት መሸጥ አንሶን ለመገደልና ለመደምሰስ ቀርበናል፤ ለባርነት ከመሸጥ የከፋ ነገር ባይደርስብን ኖሮ፥ ዝም ባልኩና እርስዎን ለማስቸገር ባልደፈርኩ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ ልንጠፋና ከምድር ገጽ ልንደመሰስ ተፈርዶብናል!” ስትል መለሰችለት።
5ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ “ይህን ለማድረግ የደፈረ ማን ነው? ለመሆኑ ይህ ሰው የት ይገኛል?” ሲል ንግሥት አስቴርን ጠየቃት።
6አስቴርም “ጠላታችንና ሞት የፈረደብንማ ሃማን የተባለው ይህ ክፉ ሰው ነው!” አለችው።
ሃማንም እጅግ በመደንገጥ አንዴ ወደ ንጉሡ፥ አንዴ ወደ ንግሥቲቱ ይመለከት ነበር፤ 7ንጉሡም እጅግ ተቈጣና ግብዣውን ትቶ በመነሣት ከነበረበት ክፍል ወጥቶ ወደ ቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ሄደ፤ ንጉሡ በዚህ ጥፋት ሊቀጣው የወሰነ መሆኑን ሃማን ተገንዝቦ ስለ ነበር ሕይወቱን ታተርፍለት ዘንድ ንግሥት አስቴርን ለመማጠን ወደ ኋላ ቀረ። 8ምሕረትም ለመለመን አስቦ ንግሥት አስቴር በተቀመጠችበት ድንክ አልጋ ላይ በግንባሩ ተደፋ፤ ንጉሡም ከአትክልቱ ቦታ ተመልሶ ወደ ክፍሉ በገባ ጊዜ ይህን በማየቱ እጅግ ተቈጥቶ “ይህ ሰው በገዛ ቤተ መንግሥቴ ዐይኔ እያየ ንግሥቲቱን ሊደፍር ይፈልጋል እንዴ?” ሲል ጮኸበት።
ንጉሡም ገና ይህን እንደ ተናገረ ወዲያውኑ ጃንደረቦቹ የሃማንን ፊት ሸፈኑ። 9ከእነርሱም አንዱ ሐርቦና የተባለው ጃንደረባ “ንጉሥ ሆይ! ሃማን እኮ ከዚህ ሁሉ አልፎ አንተን ከሞት ያዳነህን መርዶክዮስን በስቅላት ሞት ለመቅጣት አስቦ የተከለው እንጨት በቤቱ ይገኛል፤ የእንጨቱም ርዝመት ኻያ ሁለት ሜትር ነው!” ሲል ተናገረ።
ንጉሡም “ሃማንን ወስዳችሁ በዚያ እንጨት ላይ ስቀሉት!” ሲል ትእዛዝ ሰጠ።
10ስለዚህም ሃማን መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው እንጨት ላይ ተሰቀለ፤ ከዚያም በኋላ የንጉሡ ቊጣ በረደ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ