የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 3

3
ሃማን አይሁድን ለማጥፋት ሤራ መጠንሰሱ
1ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ የሃመዳታ ልጅ የሆነውን አጋጋዊውን ሐማንን ከሌሎቹ መኳንንት ሁሉ በላይ ክብሩን በማስበለጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመው። #3፥1 አጋጋዊ፦ ይህ አጋግ የተባለው ሰው ነቢዩ ሳሙኤል የገደለው በመሆኑ ጠላትነቱ የዘር እንጂ በመርዶክዮስ ምክንያት ብቻ አልነበረም፤ 1ኛ ሳሙኤል ም. 15፥33። 2ንጉሡም በግዛቱ ሥር ያሉ ባለሥልጣኖች ሁሉ በጒልበታቸው ተንበርክከው እየሰገዱ እጅ በመንሣት ያከብሩት ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ሁሉ እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ ይህን ለማድረግ እምቢ ያለ መርዶክዮስ ብቻ ነበር። 3በቤተ መንግሥት ሥራ ላይ የተመደቡ ሌሎች ባለሥልጣኖች መርዶክዮስን “የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ?” እያሉ፥ 4ከቀን ወደ ቀን ሐሳቡን ለማስቀየር ይጥሩ ነበር፤ እርሱ ግን ሊሰማቸው አልወደደም፤ እንዲያውም እኔ አይሁዳዊ ስለ ሆንኩ ለሃማን መስገድ አይገባኝም በማለት ቊርጥ ውሳኔውን ገለጠላቸው ከዚህ በኋላ የመርዶክዮስን ትዕቢት እንዴት መታገሥ ይቻላል? እያሉ በመገረም ጉዳዩን ለሃማን ነገሩት። 5ሃማንም መርዶክዮስ ተንበርክኮ የማይሰግድለት መሆኑን ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 6በተለይም መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን በተረዳ ጊዜ መርዶክዮስን ብቻ መግደል በቂ እንዳልሆነ ተገነዘበ፤ ስለዚህም በመላው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉትን የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድን ሁሉ ለማጥፋት ዕቅድ አወጣ።
7አርጤክስስ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ ኒሳን ተብሎ በሚጠራው የመጀመሪያው ወር ፑሪም ተብሎ የተሠየመው ዕጣ መጣል እንዲጀመርና አይሁድን ለማጥፋት የተጠነሰሰውን ሤራ በሥራ ላይ ለማዋል አመቺ የሚሆነው ወርና ቀን የትኛው እንደ ሆነ ተለይቶ እንዲታወቅ ትእዛዝ ሰጠ፤ በዕጣውም መሠረት አዳር ተብሎ የሚጠራው ዐሥራ ሁለተኛው ወር በገባ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን እንዲሆን ተወሰነ።
8ስለዚህም ሃማን ለንጉሥ አርጤክስስ እንዲህ ሲል አስረዳው፦ “በንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ ግዛት ውስጥ በየአገሩ ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ፤ ይህም ሕዝብ ከሌሎች አሕዛብ የተለየ ሕግ አለው፤ ከዚህም በላይ ለንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ሕግ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ ታዲያ፥ ይህን ዐይነቱን ሕዝብ ዝም ብለህ ብትታገሥ ለአንተ አደገኛ ነገር ይሆንብሃል፤ 9ንጉሥ ሆይ! ይህ ሕዝብ በሞት የሚቀጣበትን ዐዋጅ ለማስተላለፍ መልካም ፈቃድህ ይሁን፤ ይህን ብታደርግ እኔ ለንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ አስተዳደር መርጃ ይሆን ዘንድ ሦስት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት ገቢ እንደማደርግ ቃል እገባለሁ።”
10ንጉሡም ዐዋጆችን ሁሉ ይፋ የሚያደርግበትን የቀለበት ማኅተም ወስዶ ለአጋጋዊው ለሃመዳታ ልጅ የአይሁድ ጠላት ለሆነው ለሃማን ሰጠው። 11ንጉሡም “እነሆ ሕዝቡ ከነንብረታቸው የአንተ ስለ ሆኑ በእነርሱ ላይ የወደድከውን አድርግ” ሲል ፈቀደለት።
12ስለዚህ የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ሃማን የንጉሡን ጸሐፊዎች ጠርቶ ዐዋጁ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጒሞ፥ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሚገኘው የአጻጻፍ ሥርዓት ሁሉ በመዘጋጀት፥ ወደ አገረ ገዢዎችና ወደ ባለሥልጣኖች ሁሉ እንዲላክ ያደርጉ ዘንድ አዘዘ፤ ዐዋጁም በንጉሥ አርጤክስስ ስም ተጽፎ የቀለበቱ ማኅተም ተደርጎበት ተላለፈ። 13ፈጣኖች የሆኑ ሯጮችም ይህን ዐዋጅ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ወደሚገኙት አገሮች ሁሉ እንዲያደርሱ ተላኩ፤ በዐዋጁም ውስጥ አዳር ተብሎ በሚጠራው በዐሥራ ሁለተኛው ወር፥ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን መላውን የአይሁድ ወጣት፥ ሽማግሌ፥ ሴት፥ ወንድ ሳይቀር ሕፃናትንም ጭምር እንዲገድሉ፥ እንዲያጠፉና እንዲደመሰሱ የሚያዝ ቃል ነበረበት፤ ንብረታቸውም ሁሉ እንዲዘረፍ ትእዛዝ ወጥቶ ነበር። 14ያ የተቀጠረው ቀን ሲደርስ ሰው ሁሉ ይዘጋጅ ዘንድ ደብዳቤዎቹ ሰው ሁሉ ሊያይ በሚችልበት ቦታ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ሁሉ እንዲለጠፉ ንጉሡ አዘዘ።
15በንጉሡም ትእዛዝ ዐዋጁ ሱሳ ተብላ በምትጠራው መናገሻ ከተማ በይፋ ተገልጦ እንዲታይ ተደረገ፤ ፈጣኖች የሆኑ ሯጮችም ወደየአገሩ መልእክቱን አደረሱ፤ መናገሻ ከተማይቱ ሱሳ ታውካ ሳለች፥ ንጉሡና ሃማን በአንድነት ተቀምጠው የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ