መጽሐፈ አስቴር 2:5-11

መጽሐፈ አስቴር 2:5-11 አማ05

እዚያም በሱሳ ከተማ የሚኖር መርዶክዮስ ተብሎ የሚጠራ አንድ አይሁዳዊ ነበር፤ እርሱ የያኢር ልጅ ሲሆን ከብንያም ነገድ የቂስና የሺምዒ ዘር ነበር። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ከኢየሩሳሌም ማርኮ በወሰደው ጊዜ ከእነርሱ አንዱ መርዶክዮስ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። እርሱም በዕብራይስጥ ሀዳሳ የተባለችውን የአጐቱን ልጅ አስቴርን ያሳድግ ነበር፤ እርስዋም ቁመናዋ የተስተካከለ እጅግ ውብ ልጃገረድ ነበረች፤ ወላጆችዋም ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ መርዶክዮስ ወደ ቤቱ በመውሰድ ልክ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ በመንከባከብ አሳደጋት። ንጉሡ ዐዋጁን ባስተላለፈ ጊዜ ወደ ሱሳ ከተማ ከመጡት ብዙ ልጃገረዶች መካከል አንድዋ አስቴር ነበረች፤ እርስዋም ወደ ቤተ መንግሥት ተወስዳ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ኀላፊ በሆነው በሄጋይ ቊጥጥር ሥር እንድትሆን ተደረገ። አስቴርም ሄጋይን ደስ አሰኘችው፤ በፊቱም ሞገስ አገኘች፤ ጊዜም ሳያባክን ወዲያውኑ ጥሩ ምግብ እንዲሰጣትና የሰውነትዋ ቅርጽ በመታሸት እንዲስተካከል በማድረግ በቊንጅና እንክብካቤ እንድትጠበቅ ወሰነ፤ ከምርጥ ሴቶችም መኖሪያ ቤት ከሁሉ የተሻለውን ክፍል መርጦ በመስጠት ከቤተ መንግሥት የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮች ያገለግሉአት ዘንድ መደበላት። መርዶክዮስ አስቀድሞ ባሳሰባት መሠረት አስቴር አይሁዳዊት መሆንዋን በምሥጢር ትጠብቀው ነበር፤ መርዶክዮስም አስቴር በምን ሁኔታ እንዳለችና ወደ ፊት የሚገጥማት ዕድል ምን እንደሆን ለማወቅ በየቀኑ በምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት አደባባይ ፊት ለፊት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር።