የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 2

2
አስቴር ንግሥት እንደ ሆነች
1ዘግየት ብሎም የንጉሡ ቊጣ ከበረደ በኋላ እንኳ፥ ንግሥት አስጢን ስላደረገችው ነገርና በእርስዋም ላይ ስለ ተላለፈው ዐዋጅ ማሰላሰሉን ቀጠለ። 2ስለዚህም የንጉሡ የቅርብ አማካሪዎች ከዚህ የሚከተለውን ሐሳብ አቀረቡለት፤ “ውብ የሆኑ ወጣት ልጃገረዶች ለአንተ ይፈለጉልህ፤ 3በንጉሠ ነገሥትህ ግዛት በየአገሩ ባለ ሥልጣኖችን በመሾም ውብ የሆኑትን ልጃገረዶች እየመረጡ መናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ውስጥ ለአንተ የተመረጡ ሴቶች መኖሪያ ወደ ሆነው ቤት እንዲያመጡአቸው ይደረግ፤ የዚህም ቤት ኀላፊ ባደረግኸው በጃንደረባው ሄጋይ ቊጥጥር ሥር ይጠበቁ፤ የቊንጅናም እንክብካቤ ይደረግላቸው። 4ከእነርሱም መካከል በይበልጥ የምትወዳትን መርጠህ በአስጢን እግር ተተክታ ንግሥት እንድትሆን አድርግ።”
ንጉሡም ይህ ምክር መልካም መሆኑን ተመልክቶ በሥራ ላይ አዋለው።
5እዚያም በሱሳ ከተማ የሚኖር መርዶክዮስ ተብሎ የሚጠራ አንድ አይሁዳዊ ነበር፤ እርሱ የያኢር ልጅ ሲሆን ከብንያም ነገድ የቂስና የሺምዒ ዘር ነበር። 6የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ከኢየሩሳሌም ማርኮ በወሰደው ጊዜ ከእነርሱ አንዱ መርዶክዮስ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። #2ነገ. 24፥10-16፤ 2ዜ.መ. 36፥10። 7እርሱም በዕብራይስጥ ሀዳሳ የተባለችውን የአጐቱን ልጅ አስቴርን ያሳድግ ነበር፤ እርስዋም ቁመናዋ የተስተካከለ እጅግ ውብ ልጃገረድ ነበረች፤ ወላጆችዋም ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ መርዶክዮስ ወደ ቤቱ በመውሰድ ልክ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ በመንከባከብ አሳደጋት።
8ንጉሡ ዐዋጁን ባስተላለፈ ጊዜ ወደ ሱሳ ከተማ ከመጡት ብዙ ልጃገረዶች መካከል አንድዋ አስቴር ነበረች፤ እርስዋም ወደ ቤተ መንግሥት ተወስዳ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ኀላፊ በሆነው በሄጋይ ቊጥጥር ሥር እንድትሆን ተደረገ። 9አስቴርም ሄጋይን ደስ አሰኘችው፤ በፊቱም ሞገስ አገኘች፤ ጊዜም ሳያባክን ወዲያውኑ ጥሩ ምግብ እንዲሰጣትና የሰውነትዋ ቅርጽ በመታሸት እንዲስተካከል በማድረግ በቊንጅና እንክብካቤ እንድትጠበቅ ወሰነ፤ ከምርጥ ሴቶችም መኖሪያ ቤት ከሁሉ የተሻለውን ክፍል መርጦ በመስጠት ከቤተ መንግሥት የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮች ያገለግሉአት ዘንድ መደበላት።
10መርዶክዮስ አስቀድሞ ባሳሰባት መሠረት አስቴር አይሁዳዊት መሆንዋን በምሥጢር ትጠብቀው ነበር፤ 11መርዶክዮስም አስቴር በምን ሁኔታ እንዳለችና ወደ ፊት የሚገጥማት ዕድል ምን እንደሆን ለማወቅ በየቀኑ በምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት አደባባይ ፊት ለፊት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር።
12ሴቶቹ የቊንጅና እንክብካቤ እየተደረገላቸው የሚቆዩት እስከ አንድ ዓመት ነበር፤ ይኸውም የሰውነታቸው ቅርጽ እንዲስተካከል ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በከርቤና በዘይት፥ እንደገናም ለቀሪዎቹ ስድስት ወራት ባልሳም በተባለ ጣፋጭ ሽቶ ይታሻሉ፤ ከዚያም በኋላ እያንዳንድዋ ልጃገረድ በየተራ ወደ ንጉሥ አርጤክስስ ዘንድ እንድትገባ ይደረጋል። 13ምርጥ ሴቶች ከሚኖሩበት ቤት ወጥታ ወደ ቤተ መንግሥት በምትገባበትም ጊዜ ልትለብስ የምትፈልገው ልብስ ይሰጣት ነበር። 14እርስዋም ሌሊቱን ከንጉሡ ጋር ዐድራ በማግስቱ ወደ ሌላ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ትወሰዳለች፤ እዚያም የንጉሡ ቊባቶች ኀላፊ በሆነው በጃንደረባው በሻዕሸጋዝ ቊጥጥር ሥር ትሆናለች፤ በንጉሡ ዘንድ ተወዳጅነትን አግኝታ እርሱ ስምዋን ጠርቶ እንደገና እንድትመጣለት ካልጠየቀ በቀር ዳግመኛ ወደ እርሱ አትቀርብም።
15በዚህ ዐይነት አስቴር ወደ ንጉሡ ፊት የምትቀርብበት ጊዜ ደረሰ፤ ይህችም አስቴር የአቢኀይል ልጅ፥ እንደ ልጁ አድርጎ ያሳደጋት የመርዶክዮስ የአጐት ልጅ የነበረችውና ባያት ሁሉ ዘንድ ሞገስን ያገኘች ነበረች፤ እርስዋም ወደ ንጉሡ ፊት የመቅረብ ተራዋ በደረሰ ጊዜ የለበሰችው፥ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ኀላፊ የነበረው ጃንደረባው ሄጋይ እንድትለብስ የመከራትን እንጂ እርስዋ የጠየቀችውን ልብስ አልነበረም። 16ስለዚህም አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት ተብሎ በሚጠራው በዐሥረኛው ወር አስቴር ወደ ቤተ መንግሥቱ ተወሰደች። 17ንጉሡም ከሌሎቹ ልጃገረዶች ሁሉ አስበልጦ ወደዳት፤ ከሌሎቹም ሁሉ ይበልጥ በፊቱ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ እርሱም መንግሥታዊውን ዘውድ አንሥቶ በራስዋ ላይ ደፋላትና በአስጢን ቦታ አነገሣት። 18ከዚህም በኋላ ንጉሡ ስለ አስቴር ክብር ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖችና አስተዳዳሪዎች ሁሉ ጠራ፤ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በሚገኙት አገሮች ሁሉ የደስታ በዓል እንዲደረግ ዐወጀ፤ ለጋስነት የተሞላበት ንጉሣዊ ስጦታም አደረገ።
መርዶክዮስ የንጉሡን ሕይወት እንዳዳነ
19ደናግሉ ዳግመኛ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ ቤተ መንግሥት በር ላይ ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። 20አስቴርም አይሁዳዊት መሆንዋን ገና አላስታወቀችም ነበር፤ መርዶክዮስም ይህን ለማንም እንዳትናገር በጥብቅ አስጠንቅቆአት ነበር፤ እርስዋም በሕፃንነትዋ ጊዜ በእርሱ ኀላፊነት ሥር ሳለች በሁሉ ነገር ትታዘዘው እንደ ነበር አሁንም በዚህ ነገር ታዘዘችለት።
21መርዶክዮስ በቤተ መንግሥቱ በር ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ ወደ ንጉሡ መኖሪያ ክፍሎች የሚያስገቡትን በሮች ይጠብቁ የነበሩት ቢግታንና ቴሬሽ ተብለው የሚጠሩት ሁለቱ የቤተ መንግሥት ጃንደረቦች በንጉሥ አርጤክስስ ላይ በጠላትነት ተነሣሥተው ሊገድሉት ዐድመው ነበር። 22መርዶክዮስ ይህን ዐድማ በሰማ ጊዜ ለንግሥት አስቴር ነገራት፤ አስቴርም በመርዶክዮስ ስም ምሥጢሩን ለንጉሡ ነገረች። 23ምርመራም በተደረገ ጊዜ የቀረበው መረጃ እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ስለዚህም ሁለቱ ዐመፀኞች በስቅላት ሞት ተቀጡ፤ ንጉሡም ይህ ሁኔታ በንጉሠ ነገሥቱ የታሪክ መዝገብ ተጽፎ እንዲቀመጥ ትእዛዝ አስተላለፈ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ