ስለዚህ እኔ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንኩት ለእናንተ ለአሕዛብ ስል ነው። ለእናንተ ጥቅም እንዳውለው እግዚአብሔር በጸጋው የአገልግሎት ዕድል እንደ ሰጠኝ በእርግጥ ሰምታችኋል። አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍኩላችሁ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ገልጦ በራእይ አሳይቶኛል። ይህን የጻፍኩላችሁንም ስታነቡ ስለ ክርስቶስ ምሥጢር እኔ ያስተዋልኩትን ለመረዳት ትችላላችሁ። ይህም ምሥጢር በእግዚአብሔር መንፈስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ነቢያቱ አሁን እንደተገለጠው ዐይነት ባለፉት ዘመናት ለነበሩት ሰዎች አልተገለጠም። ይህም የሚያመለክተው አሕዛብ ከአይሁድ ጋር የርስቱ ወራሾችና የአንድ አካል ክፍሎች ሆነው እግዚአብሔር ለሰጠው ተስፋ በወንጌል አማካይነት በኢየሱስ ክርስቶስ ተካፋዮች መሆናቸውን ነው። እግዚአብሔር በኀይሉ አሠራር በሰጠኝ የጸጋ ስጦታ እኔም የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኜአለሁ። እኔ ከቅዱሳን ሁሉ የማንስ ብሆንም እንኳ ወሰን የሌለውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ እንዳበሥር በእግዚአብሔር ጸጋ ይህ ዕድል ተሰጠኝ። እንዲሁም ባለፉት ዘመናት ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ተሰውሮ ስለ ነበረው ምሥጢር የእግዚአብሔር ዕቅድ ምን እንደ ሆነ ለሁሉ እንድገልጥ ጸጋ ተሰጠኝ። ይህም የሆነው በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት በሰማይ ያሉት አለቆችና ባለሥልጣኖች የእግዚአብሔርን ጥበብ በየመልኩ እንዲያውቁ ነው። እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የፈጸመው በዘለዓለማዊው ዕቅዱ መሠረት ነው። የክርስቶስ በመሆናችንና በእርሱ በማመናችን በእግዚአብሔር ፊት በድፍረትና በመተማመን መቅረብ እንችላለን። እኔ ስለ እናንተ የምቀበለው መከራ ክብራችሁ ነው፤ ስለዚህ በመከራዬ ምክንያት ተስፋ አትቊረጡ ብዬ እለምናችኋለሁ። እንግዲህ በእግዚአብሔር አብ ፊት በጒልበቴ ተንበርክኬ የምጸልየው በዚህ ምክንያት ነው። በሰማይና በምድር ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ እውነተኛ ስሙን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ውስጣዊውን ሰውነታችሁን የሚያጠነክር ኀይል በመንፈሱ አማካይነት ከክብሩ ባለጸግነት እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ። እንዲሁም ክርስቶስ በእምነት በልባችሁ እንዲኖርና እናንተም ሥር ሰዳችሁ በፍቅር የጸናችሁ እንድትሆኑ እጸልያለሁ። ደግሞም የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱና ርዝመቱ፥ ከፍታውና ጥልቀቱ፥ ምን ያኽል መሆኑን ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ማስተዋል እንድትችሉና ይህን ከሰው ዕውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር እንድታውቁ በእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ለመሞላትም እንድትበቁ እጸልያለሁ። ስለዚህ በእኛ ውስጥ በሚሠራው ኀይሉ አማካይነት ከምንለምነውና ከምናስበው በላይ እጅግ አትረፍርፎ ሊያደርግ ለሚቻለው አምላክ፥ ለእርሱ በቤተ ክርስቲያንና በኢየሱስ ክርስቶስ በዘመናት ሁሉ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች