የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1:1-23

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1:1-23 አማ05

በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ታማኞች ለሆኑት፥ በኤፌሶን ለሚገኙት ቅዱሳን፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። በሰማይ ባለው መንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን። ቅዱሳንና ነቀፋ የሌለብን ሆነን በፊቱ እንድንገኝ ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ መረጠን። እግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ሆኖ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ በፍቅሩ መረጠን። ይህንንም ያደረገው በተወደደው ልጁ አማካይነት በነጻ የሰጠን ክቡር ጸጋ እንዲመሰገን ነው። ከእግዚአብሔር ጸጋ ሙላት የተነሣ በልጁ ደም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አገኘን። ጸጋውንም በጥበብና በዕውቀት ሁሉ አብዝቶ አፈሰሰልን። እግዚአብሔር በቸርነቱ በክርስቶስ አማካይነት አስቀድሞ ባቀደው መሠረት የፈቃዱን ምሥጢር እንድናውቅ አደረገ። ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር በሥራ ላይ የሚያውለው ዕቅድ በሰማይና በምድር ያሉት ፍጥረቶች ሁሉ ተጠቃለው በአንዱ በክርስቶስ ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ ነው። ሁሉን ነገር በራሱ ፈቃድ የሚሠራ እግዚአብሔር አስቀድሞ በዐቀደልን መሠረት በክርስቶስ አማካይነት የእርሱ ወገኖች እንድንሆን መረጠን። ይህም የሆነው ክርስቶስን ተስፋ በማድረግ መጀመሪያዎች የሆንነው የእግዚአብሔርን ክብር በምስጋና እንድንገልጥ ነው። እናንተም የመዳናችሁ መልካም ዜና የሆነውን የእውነት ቃል በሰማችሁ ጊዜ በክርስቶስ አምናችኋል፤ እንዲሁም እርሱ ሊሰጣችሁ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል። ይህ መንፈስ ለክብሩ ምስጋና እንዲሆን እግዚአብሔር የራሱ የሆኑትን በሙሉ እስኪዋጅ ድረስ ልናገኝ ላለው ርስታችን መያዣችን ነው። ስለዚህ በጌታ በኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምቼ እናንተን በጸሎቴ እያስታወስኩ በእናንተ ምክንያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረቤን አላቋርጥም። ክብር የሚገባው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔርን በይበልጥ ታውቁ ዘንድ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ። ለምን ዐይነት ተስፋ እንደ ተጠራችሁና ቅዱሳን የሚወርሱት ክቡር ርስት ምን ያኽል ብዙ እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልቡናችሁ ዐይን እንዲበራላችሁ እጸልያለሁ። የማይለካው ታላቅ ኀይሉ ለእኛ ለምናምነው ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ታውቁ ዘንድ እጸልያለሁ፤ ይህንንም ታላቅ ኀይሉን በተግባር ያሳየው ከሞት አስነሥቶ በሰማይ በቀኙ ባስቀመጠው በክርስቶስ አማካይነት ነው። እግዚአብሔር አብ ክርስቶስን በሰማይ በቀኙ ያስቀመጠውም ከማንኛውም ግዛትና ሥልጣን ከኀይልና ጌትነት በላይ እንዲሁም በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዓለም ከስም ሁሉ በላይ የሆነውን ክቡር ስም በመስጠት ነው። ሁሉንም ነገር በሥልጣኑ ሥር አድርጎ አስገዛለት፤ በቤተ ክርስቲያንም ከሁሉ በላይ እንዲሆን ራስ አደረገው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፤ ክርስቶስም በቤተ ክርስቲያንና በሌላውም ሁሉ የመላ ነው።