መጽሐፈ መክብብ 3
3
ለሁሉም ጊዜ አለው
1በዚህ ዓለም ለሚፈጸም ለማናቸውም ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የወሰነለት ዘመንና ጊዜ አለው፤
2ስለዚህም እግዚአብሔር በወሰነው መሠረት፥
ለመወለድ ጊዜ አለው፤
ለመሞትም ጊዜ አለው፤
ለመትከል ጊዜ አለው፤
ለመንቀል ጊዜ አለው።
3ለመግደል ጊዜ አለው፤
ለመፈወስም ጊዜ አለው፤
ለመገንባት ጊዜ አለው፤
ለማፍረስም ጊዜ አለው።
4ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤
ለሐዘን ጊዜ አለው፤
ለመጨፈርም ጊዜ አለው።
5ድንጋይ ለመበተን ጊዜ አለው፤
ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤
ለማቀፍ ጊዜ አለው፤
ለመለያየትም ጊዜ አለው።
6ለመፈለግ ጊዜ አለው፤
የጠፋውን ላለመፈለግ ጊዜ አለው፤
ለመጠበቅ ጊዜ አለው፤
ለመጣልም ጊዜ አለው።
7ለመቅደድ ጊዜ አለው፤
ለመስፋትም ጊዜ አለው፤
ለዝምታ ጊዜ አለው፤
ለንግግርም ጊዜ አለው።
8ለመውደድ ጊዜ አለው፤
ለመጥላትም ጊዜ አለው፤
ለጦርነት ጊዜ አለው፤
ለሰላምም ጊዜ አለው።
9ታዲያ፥ ሠራተኛ ከድካሙ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? 10የሰው ልጆች እንዲደክሙበት እግዚአብሔር የሰጣቸውን የከባድ ሥራ ጭነት ተመለከትኩ። 11እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ በመወሰን ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ ሠርቶታል፤ ዘለዓለማዊነትንም በሰው ልቡና አሳድሮአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሁሉ እስከ መጨረሻ ያውቅ ዘንድ ለሰው የተሰጠው ዕውቀት ሙሉ አይደለም። 12ስለዚህ ሰው በሕይወቱ ሳለ መልካም ነገር ከማድረግና ደስ ከሚለው በቀር ሌላ የተሻለ ነገር እንደሌለ ተረድቼአለሁ። 13ሰው ጥሮ ግሮ ባገኘው የድካም ዋጋ በልቶና ጠጥቶ መደሰት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።
14እግዚአብሔር የሠራው ነገር ሁሉ ዘለዓለማዊነት እንዳለው ዐውቃለሁ፤ በእርሱ ላይ የሚጨመርበት ወይም ከእርሱ የሚቀነስ ነገር የለም፤ እግዚአብሔር ይህን ያደረገው ሰዎች እርሱን እንዲፈሩት ነው። 15የሚሆነውና መሆን የሚችለው ነገር ሁሉ ያው ቀድሞ ተደርጎ የነበረው ነው፤ እግዚአብሔር ያንኑ ቀድሞ የፈጠረውን ነገር እንዲደጋገም ያደርጋል።
በዓለም ስላለ የፍትሕ መጓደል
16ደግሞም በዓለም ላይ በቅንነትና በፍትሕ ቦታ ዐመፅና ግፍ መብዛቱን አየሁ። 17እኔም “ሁሉ ነገር የሚፈጸምበት ጊዜ ስላለው እግዚአብሔር በዐመፀኞችም ሆነ በቅኖች ላይ ይፈርዳል” ብዬ አሰብኩ። 18እንደገናም “የሰው ልጆች ከእንስሶች ምንም የማይሻሉ መሆናቸውን እንዲረዱ፥ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል” ብዬ አሰብኩ። 19በእርግጥም የሰው ልጆችና የእንስሶች ዕድል ፈንታቸው አንድ ዐይነት ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁለቱም የተፈጥሮ እስትንፋስ አንድ ዐይነት ነው፤ ታዲያ ሁለቱም ከንቱ ስለ ሆኑ ሰው ከእንስሳ አይሻልም። 20ሰውም ሆነ እንስሳ ሁለቱም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፤ ይኸውም ከዐፈር የተሠሩ በመሆናቸው ወደ ዐፈርነት ይመለሳሉ። 21ታዲያ፥ የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣና የእንስሶች ነፍስ ደግሞ ወደ መሬት እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? 22የሰው ዕድል ፈንታ ይኸው ስለ ሆነ በሚሠራው ነገር ደስ ከሚለው በቀር ሌላ የሚያደርገው ምንም ነገር እንደሌለ አስተዋልኩ፤ ከሞተም በኋላ የሚሆነውን ነገር የሚያውቅ ማንም የለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997