መጽሐፈ መክብብ 11
11
ጥበበኛ ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነገር
1እንጀራህን በውሃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀንም በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህ። 2ወደ ፊት በዓለም ላይ ምን ዐይነት ክፉ ነገር እንደሚመጣ አታውቅም፤ ስለዚህ ያለህን ሀብት በሰባት ወይም በስምንት ቦታ ከፋፍለህ አኑር።
3ደመና ብዙ ውሃ ባዘለ ጊዜ በምድር ላይ ያዘንበዋል፤ ዛፍ ወደ ደቡብም ሆነ ወደ ሰሜን ቢወድቅ በዚያው በወደቀበት ስፍራ ይኖራል። 4ነፋስን የሚጠብቅ አይዘራም፤ ደመናን የሚመለከት አያጭድም። 5የነፋስን አካሄድና የሰውም ሕይወት አፈጣጠር በእናቱ ማሕፀን እንዴት እንደሚጀመር እንደማታውቅ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እግዚአብሔር ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ማወቅ አትችልም። 6ጧትም ሆነ ማታ ዘር መዝራትህን አታቋርጥ፤ ሁሉም ይበቅል ወይም አይበቅል እንደ ሆነ የትኛው አዘራር እንደሚሻል ለይተህ ማወቅ አይቻልህም።
7ብርሃን ታይቶ አይጠገብም፤ ስለዚህ የቀንን ብርሃን እያዩ መደሰት መልካም ነው። 8ሰው የቱንም ያኽል ብዙ ዓመት ቢኖር በዚያው በተሰጠው በዕድሜው ዘመን ሁሉ ደስ ሊለው ይችላል፤ ሆኖም የዚህ ዓለም ነገር ሁሉ ከንቱ መሆኑንና ወደፊት የሚመጣበትም የጨለማ ዘመን ዘለዓለማዊ እንደ ሆነ አይዘንጋ።
ለወጣቶች የሚሆን ምክር
9ወጣት ሆይ! ወጣትነት እጅግ ግሩም ስለ ሆነ በወጣትነትህ ዘመን ደስ ይበልህ፤ በልብህም ሐሤት አድርግ፤ ዐይንህ የሚያየውንና ልብህ የሚመኘውን ሁሉ ፈጽም፤ ሆኖም ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣህ ዕወቅ።
10የወጣትነትና የብርቱ ጐልማሳነት ጊዜ ቶሎ ስለሚያልፍ ሐዘንን ከልብህ፥ ጭንቀትንም ከአእምሮህ አስወግድ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997