የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 8

8
የተስፋይቱን ምድር ስለ መውረስ የተሰጠ መመሪያ
1“በሕይወት መኖር እንድትችሉ፥ ቊጥራችሁ እንዲበዛ፥ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁ ሊሰጣቸው ቃል የገባላቸውን ምድር ለመውረስ እንድትበቁ፥ ዛሬ እኔ የሰጠኋችሁን ትእዛዝ ሁሉ በታማኝነት ጠብቁ። 2አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዞች ስለ መጠበቅህ በልብህ ያለውን ሐሳብ ያውቅ ዘንድ አንተን ለመፈተን በዚህ በረሓ አርባ ዓመት ሙሉ በመከራ ውስጥ በማሳለፍ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ። 3በራብ እንድትሠቃይ አደረገህ፤ ቀጥሎም አንተም ሆንክ የቀድሞ አባቶችህ የማታውቁትን መና አበላህ፤ ይህንንም ማድረጉ ሰው ሕይወቱ ተጠብቆለት መኖር የሚችለው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አለመሆኑን ሊያስተምርህ ነው። #ማቴ. 4፥4፤ ሉቃ. 4፥4። 4በእነዚህም አርባ ዓመቶች ውስጥ ልብስህ አላለቀም፤ ከጒዞም የተነሣ እግርህ አላበጠም። 5አባት ልጆቹን እንደሚገሥጽ አምላክህ እግዚአብሔርም አንተን የሚገሥጽህ መሆኑን አስተውል። 6እርሱን በመፍራትና የእርሱንም መንገድ በመከተል፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቅ። 7እነሆ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መልካሚቱ ለምለም ምድር ሊያስገባህ አምጥቶሃል፤ ያቺም ምድር ከሸለቆዎችና ከኮረብቶች የሚመነጩ ወንዞችና ጅረቶች፥ ፈሳሾች ምንጮችም ይገኙበታል፤ 8ስንዴና ገብስ፥ ወይንና በለስ፥ ሮማንና የወይራ ፍሬ፥ ማርም የሞላባት ናት፤ 9ምድሪቱ ሳይጓደልብህ እንጀራ የምትበላባትና ምንም ነገር የማታጣባት ናት፤ ከድንጋዮችዋ ብረት፥ ከኮረብቶችዋም መዳብ ይገኛል። 10በልተህ ትጠግባለህ፤ ይህችን ለም ምድር የሰጠህን እግዚአብሔር አምላክህንም ታመሰግናለህ።
እግዚአብሔርን ለሚረሱ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
11“እግዚአብሔር አምላክህን በመርሳት፥ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዞች፥ ደንቦችና ሥርዓቶች እንዳታፈርስ ተጠንቀቅ። 12በልተህ በምትጠግብበትና ጥሩ ቤቶች ሠርተህ በምትኖርበት ጊዜ፥ 13የከብቶችህና የበጎችህ መንጋ፥ ብርህና ወርቅህ እንዲሁም ሌላው ሀብትህ ሁሉ በበዛልህ ጊዜ፥ 14ልብህ እንዳይታበይና በባርነት ከኖርክባት ከግብጽ ምድር ያወጣህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። 15መርዘኛ እባብና ጊንጥ በሞላበት፥ አስፈሪ በሆነው በዚያ ሰፊ በረሓ መርቶሃል፤ ምንም ውሃ በማይገኝበት ደረቅ በረሓ ከጽኑ አለት ውሃን አፈለቀልህ፤ 16ሊያዋርድህና ሊፈትንህ፥ በመጨረሻም መልካም ነገር ሊያደርግልህ የቀድሞ አባቶችህ ተመግበው የማያውቁትን መና በምድረ በዳ ሰጠህ። #ሆሴዕ 13፥5-6። 17ስለዚህም ‘ባለጸጋ የሆንኩት በራሴ ኀይልና ብርታት ነው’ ብለህ ከቶ አታስብ። 18ባለጸጋ እንድትሆን ኀይልና ብርታት የሰጠህ እግዚአብሔር አምላክህ መሆኑን አስታውስ፤ እርሱ ይህን የሚያደርግበት ምክንያት ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ ከቀድሞ አባቶችህ ጋር በመሐላ የገባውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ ነው። 19እግዚአብሔር አምላክህን ብትረሳና ትሰግድላቸውና ታገለግላቸውም ዘንድ ወደ ባዕዳን አማልክት ፊትህን ብትመልስ፥ በእርግጥ የምትጠፋ መሆንህን ዛሬውኑ አስጠነቅቅሃለሁ። 20ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝ ወደ ፊት በሄድህ መጠን ከፊትህ የሚገኙትን ሕዝቦች ሁሉ እንደሚደመስስ አንተንም ነቃቅሎ ያጠፋሃል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ