“የተኰላሸ ወይም የተሰለበ ሰው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ አባል አይሁን። “ከጋብቻ ውጪ ዲቃላ ሆኖ የተወለደና የእርሱም ዘር ሆኖ የተወለደ ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ገብቶ አይቈጠር። “ዐሞናዊም ሆነ ሞአባዊ ወይም የእነርሱ ዘር የሆነ ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ አባል አይሁን። እናንተ ከግብጽ ምድር ወጥታችሁ በጒዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እነርሱ እህልና ውሃ አንሰጥም ብለው ከልክለዋችሁ እንደ ነበር አይዘነጋም፤ ከዚሁም ጋር በመስጴጦምያ ፐቶር ተብላ በምትጠራው ከተማ ይኖር የነበረ የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲረግማችሁ ቀጥረውት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክህ እርሱን ማዳመጥ አልፈለገም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር አንተን ስለሚወድህ መርገሙን ወደ በረከት ለወጠው። እግዚአብሔር እናንተን ይወዳችኋል። በምትኖርበት ዘመን ሁሉ እነዚህ ሕዝቦች ባለጸጎች ሆነው በሰላም እንዲኖሩ አትርዳቸው። “ኤዶማውያን ዘመዶችህ ስለ ሆኑ አትጸየፋቸው፤ በግብጽ ምድር ስደተኛ ሆነህ ስለ ኖርክ ግብጻውያንን አትጸየፋቸው። የእነርሱም ከሦስተኛው ትውልድ በኋላ ዘሮቻቸው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ አባሎች ይሁኑ። “በጦርነት ጊዜ በጦር ሰፈር ውስጥ ስትገኙ፥ ርኩስ ነገርን ሁሉ አስወግዱ። አንድ ሰው ሌሊት በሕልሙ ከአባለ ዘሩ የፈሰሰ እርጥበት በሰውነቱ ላይ ቢገኝ ከሰፈር ወጥቶ በዚያው ይቈይ። ወደ ማታም ጊዜ ገላውን ይታጠብ፤ ጀንበር ስትጠልቅም ወደ ሰፈር ይመለስ። “የምትጸዳዱበትን ልዩ ስፍራ ከሰፈር ውጪ አዘጋጁ፤ በምትጸዳዱበት ጊዜ እዳሪ ለመቈፈርና መልሶ ለመድፈን የሚያገለግላችሁን አንካሴ ከጦር መሣሪያችሁ ጋር ያዙ። ሰፈራችሁን በሕጉ መሠረት በንጽሕና ጠብቁ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ሊጠብቃችሁና በጠላቶቻችሁም ላይ ድልን ሊያጐናጽፋችሁ በሰፈራችሁ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ፊቱን ከእናንተ እንዲመልስ የሚያደርገውን አስነዋሪ ነገር ሁሉ አታድርጉ። “አንድ ባሪያ ከጌታው በመኰብለል ወደ አንተ መጥቶ ቢጠጋ፥ ለጌታው አሳልፈህ አትስጠው። ከከተሞችህ በአንዱ በመረጠው ስፍራ ከአንተ ጋር በመካከልህ ይኑር እንጂ አታስጨንቀው። “እስራኤላዊ የሆነ ማንኛውም ወንድ ወይም ሴት የቤተ ጣዖት ተከታዮች እንደሚያደርጉት የዝሙት ሥራ አይፈጽሙ፤ እግዚአብሔር ዝሙትን ስለሚጠላ በዚህ ተግባር የተገኘ ገንዘብ የስእለትን መፈጸም የሚያመለክት ስጦታ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር አምላክህ ቤት አይግባ። “ለእስራኤላዊ ወገንህ ገንዘብ ብታበድረው ወይም ምግብ የሚሆንና ሌላም ነገር ብትሰጠው፥ ወለድ አትጠይቀው። ወለድ መጠየቅ የሚገባህ ከውጪ አገር ተወላጅ እንጂ ከእስራኤላዊ ወገንህ አይደለም፤ ይህን ሕግ ፈጽም፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሄደህ በምትወርሳት ምድር የምትሠራውን ሁሉ ይባርክልሃል። “ለእግዚአብሔር አምላክህ ስእለት በምታደርግበት ጊዜ ለመስጠት ወይም ለመፈጸም ቃል የገባህበትን ስእለት አታዘግይ፤ እግዚአብሔር አንተ የገባኸውን ቃል እንድትፈጽም ይፈልጋል፤ ስእለትህን ካልፈጸምክ ግን ኃጢአት ይሆንብሃል። ይሁን እንጂ ለእግዚአብሔር ስእለት አለማድረግ ራሱ ኃጢአት አይደለም፤ ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፍላጎትህ በተሳልከው መሠረት፥ አፍህ የተናገረውን በጥንቃቄ መፈጸም አለብህ። “በአንድ ሰው የወይን ተክል መካከል በምታልፍበት ጊዜ ከፍሬው የምትፈልገውን ያኽል ብላ፤ ነገር ግን በማናቸውም ዕቃ ከፍሬው አትውሰድ። በአንድ ሰው የእህል ማሳ ውስጥ በምታልፍበትም ጊዜ እሸቱን በእጅህ እየቈረጥህ መብላት ትችላለህ፤ ነገር ግን ሰብሉን አጭደህ አትውሰድ።
ኦሪት ዘዳግም 23 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘዳግም 23:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos