የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 23:1-25

ዘዳግም 23:1-25 NASV

ብልቱ የተቀጠቀጠ ወይም የተቈረጠ ማንኛውም ሰው ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። ዲቃላም ይሁን የዲቃላው ዘር የሆነ ሁሉ፣ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እንኳን ቢሆን ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወይም ማንኛውም የርሱ ዘር፣ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ ቢሆን ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። ምክንያቱም ከግብጽ ከወጣችሁ በኋላ በጕዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እህል ውሃ ይዘው አልተቀበሏችሁም፤ በመስጴጦምያ በምትገኘው በፐቶር ይኖር የነበረውን የቢዖር ልጅ በለዓምን አንተን እንዲረግም በገንዘብ ገዙት። ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን አልሰማውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ስለሚወድድህ ርግማኑን በረከት አደረገልህ። በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ሰላምን ለእነርሱ አትመኝ። ወንድምህ ስለ ሆነ ኤዶማዊውን አትጸየፈው፤ መጻተኛ ሆነህ በአገሩ ኖረሃልና ግብጻዊውን አትጥላው። ለእነርሱ የተወለዱላቸው የሦስተኛው ትውልድ ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ መግባት ይችላሉ። ጠላትህን ለመውጋት ወጥተህ በሰፈርህ ጊዜ፣ ከማናቸውም ርኩሰት ራስህን ጠብቅ። ከመካከላችሁ ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር፣ ከሰፈር ወጥቶ እዚያው ይቈይ። እየመሸ ሲመጣ ግን ገላውን ይታጠብ፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ወደ ሰፈሩ ይመለስ። ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ። ከትጥቅህም ጋራ መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቈፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት። አምላክህ እግዚአብሔር ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን። አንድ ባሪያ ከአሳዳሪው ኰብልሎ ወደ አንተ ቢመጣ፣ ለአሳዳሪው አሳልፈህ አትስጠው። ደስ በሚያሠኘው ቦታና ራሱ በመረጠው ከተማ በመካከልህ ይኑር፤ አንተም አታስጨንቀው። ወንድ ወይም ሴት እስራኤላዊ የቤተ ጣዖት አመንዝራ አይሁን። ለዝሙት ዐዳሪ ሴት ወይም ለወንደቃ የተከፈለውን ዋጋ ለማንኛውም ስእለት አድርገህ ለመስጠት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታምጣ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ሁለቱንም ይጸየፋቸዋልና። የገንዘብ፣ የእህል ወይም የማንኛውንም ነገር ወለድ ለማግኘት ለወንድምህ በወለድ አታበድር። ባዕድ ለሆነ ሰው ወለድ ማበደር ትችላለህ፤ ነገር ግን ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እጅህ በሚነካው በማናቸውም ነገር አምላክህ እግዚአብሔር እንዲባርክህ ለእስራኤላዊ ወንድምህ በወለድ አታበድረው። ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት ከተሳልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር አጥብቆ ከአንተ ይሻዋልና፣ ኀጢአት እንዳይሆንብህ ለመክፈል አትዘግይ። ሳትሳል ብትቀር ግን በደለኛ አትሆንም። በአንደበትህ የተናገርኸውን ሁሉ ለመፈጸም ጠንቃቃ ሁን፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በገዛ አንደበትህ ፈቅደህ ስእለት ተስለሃልና። ወደ ባልንጀራህ የወይን ተክል ቦታ በምትገባበት ጊዜ፣ ያሠኘህን ያህል መብላት ትችላለህ፤ ነገር ግን አንዳችም በዕቃህ አትያዝ። ወደ ባልንጀራህ ዕርሻ በምትገባበት ጊዜ፣ እሸት መቅጠፍ ትችላለህ፤ በሰብሉ ላይ ግን ማጭድ አታሳርፍበት።