ትውልዱ ሜዶናዊ የሆነው የአርጤክስስ ልጅ ዳርዮስ በባቢሎን ነገሠ። በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተመለከትኩ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ በነገረው መሠረት ኢየሩሳሌም ፍርስራሽ ሆና የምትቈይባት ዘመን ሰባ ዓመት መሆኑን ዐወቅሁ። ማቅ ለብሼና ዐመድ ላይ ተቀምጬ በመጾም ጸሎቴንና ልመናዬን ለማቅረብ ፊቴን ወደ ጌታ እግዚአብሔር መለስኩ። ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር በመናዘዝ እንዲህ ስል ጸለይኩ፦ “ለሚወዱህና ትእዛዞችህን ለሚጠብቁ ቃል ኪዳንህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅና መፈራት የሚገባህ አንተ ጌታ እግዚአብሔር ነህ። “እኛ ግን ክፉዎችና ዐመፀኞች ሆነን ኃጢአት በመሥራት በድለናል፤ ሕግህንና ትእዛዞችህን ከመፈጸም ቸል ብለናል። ለንጉሦቻችን፥ ለገዢዎቻችን፥ ለቀደሙት አባቶቻችንና በምድሪቱ ለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ በስምህ የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አላዳመጥንም። ጌታ ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፤ ነገር ግን ለአንተ ታማኞች ባለመሆናችን፥ እኛ በምድር ሁሉ ላይ የበተንከን በቅርብና በሩቅ ያለን የይሁዳ ሕዝብ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና መላዋ የእስራኤል ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ኀፍረት ደርሶብናል። ጌታ ሆይ! እኛ ሁላችን አንተን ስለ በደልን እኛ፥ ንጉሦቻችን፥ ገዢዎቻችንና የቀድሞ አባቶቻችን ኀፍረት ደርሶብናል። ጌታ አምላካችን ሆይ፥ ምንም እኛ በአንተ ላይ ብናምፅ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህ። እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! ሕጎችህን በመጠበቅ ታዛዦች ሆነን አልተገኘንም፤ በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካይነት የሰጠኸንን ትእዛዞች አልጠበቅንም። እስራኤላውያን ሁሉ ሕግህን ተላለፉ፤ የተናገርከውን ሁሉ ማዳመጥ እምቢ አሉ፤ አንተን ስለ በደልን በአገልጋይህ በሙሴ በኩል የተሰጠውን ሕግ በመሐላ የተገለጠውን ርግማን ሁሉ በእኛ ላይ አመጣህብን። በእኛና በመሪዎቻችን ላይ ታላቅ መከራ እንደምታመጣብን የተናገርከው ሁሉ እንዲፈጸምብን አደረግህ፤ ስለዚህም በምድር ላይ ካሉ አገሮች ሁሉ የኢየሩሳሌምን ያኽል ቅጣት የደረሰበት ከቶ የለም። በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት ይህን ሁሉ መከራ በእኛ ላይ አመጣህ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፥ ይህም ሁሉ ሆኖ ከኃጢአታችን በመመለስና እውነትን በመከተል የአንተን ምሕረት ለማግኘት ወደ አንተ አልጸለይንም። አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ! አንተ በሥራህ ሁሉ እውነተኛ ነህ፤ እኛ ግን ስለ አልታዘዝንህ ይህን ሁሉ መከራ አመጣህብን። “እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! ከዚህ በፊት በብርቱ ኀይልህ ሕዝብህን ከግብጽ በማውጣት ስምህ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲታወቅ አድርገሃል፥ እኛ ግን ኃጢአተኞችና በደለኞች ሆንን። ጌታ ሆይ! ስለ ፈጸምካቸው የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ብለህ ከተቀደሰችው ተራራህ ከኢየሩሳሌም ቊጣህንና መዓትህን እንድታነሣ እንለምንሃለን፤ በኃጢአታችንና በአባቶቻችንም በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በጐረቤቶቻችን ሁሉ መካከል ተዋርደዋል። አምላክ ሆይ! ጸሎቴንና ልመናዬን ስማ፤ ስለ ስምህ ስትል ለፈረሰው ቤተ መቅደስህ ራራ። አምላክ ሆይ! እባክህ አድምጠኝ፤ የእኛን ችግርና በስምህ የምትጠራውን ከተማ ጥፋት ተመልከት፤ ወደ አንተ የምንጸልየው የአንተን ምሕረት በመተማመን እንጂ በእኛ መልካም ሥራ በመመካት አይደለም። እግዚአብሔር ሆይ! ስማን! እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር በለን! እባክህ አድምጠን! ሥራህንም ግለጥ! አምላክ ሆይ! አትዘግይ፤ ይህች ከተማና ይህ ሕዝብ በስምህ የተጠሩ ናቸው።”
ትንቢተ ዳንኤል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዳንኤል 9:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos