ትንቢተ ዳንኤል 7
7
ለዳንኤል የተገለጠለት ስለ አራቱ አራዊት ራእይና ትርጒሙ
(7፥1—12፥13)
1የባቢሎን ንጉሥ ብልጣሶር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት በአልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ፤ ዳንኤል ሕልምና ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ያየውን ሕልም ጻፈ።
2እርሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ዳንኤል ከአራቱ ማእዘን የተነሣ ነፋስ ታላቁን ባሕር ሲያናውጥ ሌሊት በራእይ አየሁ። 3አራት የተለያዩ ታላላቅ አውሬዎች ከባሕሩ ወጡ። #ራዕ. 13፥1፤ 17፥8። 4የመጀመሪያው አውሬ አንበሳ ይመስል ነበር፤ እርሱም እንደ ንስር ያሉ ክንፎች ነበሩት፤ እኔም እየተመለከትኩት ክንፎቹ ተነቃቀሉ፤ አውሬውም ቀና ብሎ እንደ ሰው በሁለት እግሮቹ ቆመ፤ ሰብአዊ አእምሮም ተሰጠው።
5“ሁለተኛው አውሬ በኋላ እግሮቹ ሸብረክ ብሎ እንደ ቆመ ድብ ይመስል ነበር፤ በጥርሶቹም ሦስት የጐድን አጥንት ነክሶ ይዞአል፤ ‘የፈለግኸውን ያኽል ሥጋ ብላ!’ የሚል ድምፅም ተነገረው።
6“ይህንን በመመልከት ላይ ሳለሁ እነሆ፥ ሌላ ነብር የሚመስል አውሬ ወጣ፤ እርሱም የወፍ ክንፎች የሚመስሉ አራት ክንፎች በጀርባው ላይ ነበሩት፤ አራት ራሶችም ነበሩት፤ የገዢነት ሥልጣንም ተሰጠው። #ራዕ. 13፥2።
7“ከዚያ በኋላ አራተኛውን አውሬ አየሁ፤ እርሱም አስፈሪ፥ አስደንጋጭና በጣም ኀይለኛ ነበር፤ ይህም አውሬ የሚቦጫጭቅባቸውና የሚሰባብርባቸው ታላላቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት። የተረፈውንም በእግሮቹ ይረግጠው ነበር፤ ካለፉትም አውሬዎች ሁሉ የተለየ ሆኖ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት። #ራዕ. 12፥3፤ 13፥1። 8እኔም ስለ ቀንዶቹ በማሰላሰል ላይ ሳለሁ ከቀንዶቹ መካከል ሌላ አንድ ትንሽ ቀንድ ወጣ፤ ለእርሱም ቦታ ለመልቀቅ ከፊተኞቹ ቀንዶች ሦስቱ ተነቀሉ፤ ይህም ትንሽ ቀንድ የሰው ዐይኖችና በትዕቢት የሚናገር አንደበት ነበረው። #ራዕ. 13፥5-6።
ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖረው የተገለጠ ራእይ
9“እኔም እየተመለከትኩ ሳለሁ ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ያ ጥንታዊው በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ፥ ጠጒሩም እንደ ነጭ ሱፍ ነበር፤ ዙፋኑና የዙፋኑ መንኰራኲር እንደሚነድ እሳት ይንበለበሉ ነበር። #ራዕ. 20፥4፤ 1፥14። 10የእሳትም ምንጭ ከዙፋኑ ፊት ይፈልቅ ነበር፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ አገልጋዮች ነበሩት፤ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ችሎት ተጀመረ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። #ራዕ. 5፥11፤ 20፥12።
11“ቀንዱ የሚናገረውን የዕብሪታዊ ንግግር ድምፅ ሰምቼ ተመለከትኩ፤ እየተመለከትኩም ሳለ አውሬው ተይዞ ከተገደለ በኋላ ወደ እሳት በመጣል አካሉ እንዲጠፋ ተደረገ። 12ሌሎቹም አውሬዎች ሥልጣናቸውን ተነጠቁ፤ ይሁን እንጂ ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው።
13“በሌሊትም ራእይ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ተከቦ ሲመጣ አየሁ፤ ወደዚያ ወደ ዘለዓለማዊው ፊት አቀረቡት። #ማቴ. 24፥30፤ 26፥64፤ ማር. 13፥26፤ 14፥62፤ ሉቃ. 21፥27፤ ራዕ. 1፥7፤13፤ 14፥14። 14በልዩ ልዩ አገር የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ያገለግሉት ዘንድ ሥልጣን፥ ክብርና ንጉሥነት ተሰጠው፤ ግዛቱም የማይጠፋ ዘለዓለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም። #ራዕ. 11፥15።
የራእዩ ትርጒም
15“እኔ ዳንኤል ባየሁት ራእይ ተጨንቄ መንፈሴ ታወከ። 16እዚያም ቆመው ከነበሩት ወደ አንዱ ቀረብ ብዬ የዚህን ሁሉ እውነት ትርጒም ጠየቅሁት፤ እርሱም የዚህን ሁሉ ትርጒም ነገረኝ። 17እንዲህም አለኝ፦ ‘እነዚህ አራት ታላላቅ አውሬዎች በምድር ላይ የሚነሡ አራት መንግሥታት ናቸው። 18ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን መንግሥቱን ወርሰው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የራሳቸው እንዲሆን ያደርጉታል።’ #ራዕ. 22፥5።
19“ከዚህ በኋላ ከሌሎቹ አውሬዎች ሁሉ ልዩ ስለ ነበረው ስለ አራተኛው አውሬ በይበልጥ ለማወቅ ፈለግኹ፤ ይህ አውሬ እጅግ አስፈሪ የሆነ፥ ዐድኖ ያገኘውን ሁሉ በብረት ጥርሶቹና በነሐስ ጥፍሮቹ ሰባብሮና ቦጫጭቆ የሚበላ፥ የተረፈውንም በእግሩ የሚረጋግጥ ነበር። 20ደግሞም በዚህ አውሬ ራስ ላይ ስለ ነበሩት ዐሥር ቀንዶችና በኋላ ስለ በቀለው ትንሽ ቀንድ፥ እንዲሁም ለትንሹ ቀንድ ቦታ ለመተው ተነቃቅለው ስለ ወደቁት ሦስት ቀንዶች ለማወቅ ፈለግኹ። ይህ ትንሽ ቀንድ ዐይኖችና አፍ ነበረው፤ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ አስፈሪ ሆኖ በትዕቢት ይናገር ነበር።
21“እኔም በመመልከት ላይ ሳለሁ ያ ትንሽ ቀንድ በእግዚአብሔር ቅዱሳን ላይ ጦርነት አስነሥቶ ድል አደረጋቸው። #ራዕ. 13፥7። 22ይህም የሆነው ዘለዓለማዊው መጥቶ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ፍትሕ እስከ ሰጠበት ጊዜ ድረስ ነው፤ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወርሱበት ጊዜ ደረሰ። #ራዕ. 20፥4።
23“እርሱም ትርጒሙን እንዲህ ሲል አስረዳኝ፤ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛ መንግሥት ነው፤ ይህ መንግሥት ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ በመሆኑ ምድርን ሁሉ በመውረር ረግጦና ቀጥቅጦ ይገዛል። 24ዐሥሩ ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡት ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያን በኋላ ከበፊተኞቹ ነገሥታት የተለየ ሌላ ንጉሥ ተነሥቶ ከዐሥሩ መንግሥታት ሦስቱን ይገለብጣል፤ 25በልዑል እግዚአብሔር ላይ በመታበይ ይናገራል፤ የልዑል እግዚአብሔርንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ የተቀደሱ በዓላትንና ሕጉን ለመለወጥ ያቅዳል፤ ቅዱሳኑም ለሦስት ዓመት ተኩል በእርሱ ሥልጣን ሥር ይሆናሉ። #ራዕ. 12፥14፤ 13፥5-6። 26ከዚያን በኋላ የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ እርሱም መንግሥታዊ ሥልጣኑን ተገፎ ለዘለዓለም ይደመሰሳል፤ 27ከሰማይ ሁሉ በታች በምድር ላይ ያለ የመንግሥት ሥልጣን፥ ኀይልና ገናናነት ሁሉ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ይሰጣል፤ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የዓለም ግዛቶች ሁሉም ለእነርሱ በመታዘዝ ያገለግሉአቸዋል።’ ” #ራዕ. 20፥4፤ 22፥5።
28የሕልሙም ትርጒም እዚህ ላይ ይፈጸማል፤ እኔም ዳንኤል እጅግ ሐሳቡ አስፈራኝ፤ በመደንገጥም ፊቴ ገረጣ፤ ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር በልቤ ሰውሬ ያዝኩ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997