ትንቢተ ዳንኤል 3:19-28

ትንቢተ ዳንኤል 3:19-28 አማ05

በዚያን ጊዜ ናቡከደነፆር በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብደናጎ ላይ እጅግ ተቈጥቶ መልኩ ተለዋወጠ፤ ስለዚህ እሳቱ ከቀድሞው ይበልጥ በሰባት እጥፍ ከፍ ብሎ እንዲነድ ትእዛዝ ሰጠ። ሦስቱንም ሰዎች አስረው ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ይጥሉአቸው ዘንድ ከሠራዊቱ መካከል ብርቱ የሆኑትን አዘዘ። ስለዚህ ቀሚሳቸው፥ ሱሪያቸውና መጠምጠሚያቸው ሳይቀር ሙሉ ልብሳቸውን እንደ ለበሱ አስረው ወደሚነደው ወደ የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ጣሉአቸው። ንጉሡ በሰጠው ጥብቅ ትእዛዝ መሠረት እሳቱ በኀይል ተቀጣጥሎ ይነድ ስለ ነበር ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን ወደ እሳቱ የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን አቃጥሎ ገደላቸው። ሦስቱ ሰዎች ግን በጥብቅ እንደ ታሰሩ በእሳቱ ነበልባል ላይ ወደቁ። ከዚያን በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር በመደነቅ ፈጥኖ ተነሣና “አስረን በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት ብቻ አልነበሩምን?” ሲል አማካሪዎቹን ጠየቀ። እነርሱም “አዎ፥ ንጉሥ ሆይ!” አሉት። ንጉሡም “እነሆ፥ እኔ እሳቱ ምንም ሳይጐዳቸው ከእስራት ተፈተው በነበልባሉ ውስጥ የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አለ። ናቡከደነፆር ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ተጠግቶ “የልዑል አምላክ አገልጋዮች የሆናችሁ እናንተ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ! ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!” በማለት ተጣራ፤ እነርሱም ከእሳቱ ወጡ። ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹ፥ መኳንንቱ፥ አማካሪዎቹ ሁሉ በእነርሱ ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳው፥ ከራስ ጠጒራቸውም አንዲቱን እንኳ እንዳላቃጠለ፥ የመጐናጸፊያቸው መልክ እንዳልተለወጠና ሌላው ቀርቶ የእሳቱ ሽታ እንኳ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፦ “የሲድራቅ፥ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! እርሱ መልአኩን ልኮ እነዚህን አገልጋዮቹን አድኖአል፤ እነርሱ በአምላካቸው ተማምነው ለእርሱ ካልሆነ በቀር ለሌሎች አማልክት አንሰግድም በማለት የንጉሡን ትእዛዝ በማፍረስ ሕይወታቸውን በአደጋ ላይ ጥለውት ነበር።