ትንቢተ ዳንኤል 2:24-49

ትንቢተ ዳንኤል 2:24-49 አማ05

ከዚህ በኋላ ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ከንጉሡ ትእዛዝ ወደተሰጠው ወደ አርዮክ ሄደና “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ይልቅስ ወደ ንጉሡ አቅርበኝና የሕልሙን ትርጒም ልንገረው” አለው። አርዮክ ወዲያውኑ ዳንኤልን ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር ፊት አቀረበውና፥ “ንጉሥ ሆይ! የሕልምህን ትርጒም የሚነግርህ ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አንድ ሰው አግኝቼአለሁ” ሲል ለንጉሡ ተናገረ። ንጉሡም ብልጣሶር ተብሎ የሚጠራውን ዳንኤልን “ያየሁትን ሕልም ከነትርጒሙ ልትነግረኝ ትችላለህን?” ሲል ጠየቀው። ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! አንተ የጠየቅኸውን ምሥጢር ጠቢባንም ሆኑ አስማተኞች፤ ጠንቋዮችም ሆኑ መተተኞች ሊነግሩህ አይችሉም። ነገር ግን ምሥጢርን ሁሉ የሚገልጥ አንድ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ ለአንተ ገልጦልሃል፤ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ያየኸው ሕልምና በአእምሮህ የነበረው ራእይ የሚከተለው ነው። “ንጉሥ ሆይ! አንተ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ታሰላስል ነበር፤ ስለዚህ ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስታወቀህ። ይህም ምሥጢር ለእኔ የተገለጠልኝ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ጥበበኛ ስለ ሆንኩ አይደለም፤ ነገር ግን አንተ የሕልሙን ትርጒም እንድታውቅና በአእምሮህም ውስጥ የተመላለሰውን ሐሳብ መረዳት እንድትችል ነው። “ንጉሥ ሆይ! እጅግ የሚያንጸባርቅና ብልጭልጭታው ለማየት የሚያስፈራ ታላቅ ምስል በፊትህ ቆሞ አየህ። የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፥ ደረቱና እጆቹ ከብር፥ ሆዱና ጭኖቹ ከነሐስ፤ ቅልጥሞቹ ከብረት፥ እግሮቹ እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። አንተ ምስሉን ስትመለከት ሳለ ታላቅ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት በምስሉ እግሮች ላይ ወድቆ ሰባበራቸው። ብረቱ፥ ሸክላው፥ ነሐሱ፥ ብሩና ወርቁ ሁሉ ወዲያውኑ ተንከታክቶ በበጋ ወራት በአውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅ ሆነ፤ ምንም ሳያስቀር ነፋስ ጠራርጎ ወሰደው፤ በምስሉ ላይ የወደቀው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ከፍ ከፍ ብሎ ታላቅ ተራራ ሆነ። “እነሆ፥ ሕልሙ ይህ ነው፤ ትርጒሙም እንደሚከተለው ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ከሁሉ የምትበልጥ ንጉሠ ነገሥት ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኀይልን፤ ሥልጣንና ክብርን ሰጥቶሃል። በምድር ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎሃል፤ በሰው፥ በእንስሶችና በወፎች ላይ ሥልጣን ሰጥቶሃል፤ ስለዚህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። ከአንተ በኋላ በገናናነቱ የአንተን መንግሥት የሚያኽል አነስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ከእርሱም ቀጥሎ ዓለምን ሁሉ የሚገዛ በነሐስ የሚመሰል መንግሥት በሦስተኛ ደረጃ ይነሣል። እንደገናም ሁሉን ነገር የሚሰባብርና የሚያንከታክት እንደ ብረት የጠነከረ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ነገር ሰባብሮ እንደሚያደቅ፥ እርሱም ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቃል። እግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ መሆኑን አይተሃል፤ ይህም የሚያመለክተው ያ መንግሥት የተከፋፈለ መሆኑን ነው፤ ብረት ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ ያ መንግሥት በከፊል እንደ ብረት የጠነከረ ይሆናል። የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ብረት፥ እኩሌታው ሸክላ እንደ ሆነ እንዲሁም ያም መንግሥት በከፊል ብርቱ፥ በከፊል ደካማ ይሆናል። ብረቱ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ የእነዚያ የሁለት መንግሥታት ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በመጋባት ይደባለቃሉ፤ ሆኖም ብረት ከሸክላ መዋሐድ እንደማይችል እነርሱም አንድ መሆን አይችሉም፤ በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ግዛቱም በሌላ ሕዝብ የማይደፈር መንግሥትን ይመሠርታል፤ ይህ መንግሥት ሌሎችን መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ላይ ተፈንቅሎ በመውረድ ከብረት፥ ከነሐስ፥ ከሸክላ፥ ከብርና ከወርቅ የተሠራውን ምስል ያደቀቀውም ድንጋይ፥ ያ መንግሥት ነው፤ በዚህም ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አሳይቶሃል፤ እነሆ፥ ሕልሙ እውነት ነው፤ አስተማማኝ ትርጒሙም ይኸው ነው።” ከዚህ በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር ግንባሩ መሬት እስኪነካ ድረስ ወድቆ ለዳንኤል ሰገደለት፤ የእህል ቊርባንና ዕጣን እንዲያቀርቡለትም አዘዘ። ንጉሡም ዳንኤልን “የአንተ አምላክ ከአማልክት ሁሉ የሚበልጥ አምላክ ነው፤ የነገሥታት ሁሉ ጌታ ነው፥ ምሥጢርንም ሁሉ መግለጥ የሚችል ነው፤ ከዚህም የተነሣ ይህን ታላቅ ምሥጢር ለመግለጥ ችለሃል” አለው። ከዚህ በኋላ ንጉሡ ዳንኤልን በታላቅ ክብር ቦታ አስቀመጠው፤ ብዙ ስጦታዎችንም ሰጠው፤ በባቢሎን ግዛትም ሁሉ ላይ የበላይ ገዢ አደረገው፤ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። በዳንኤልም አሳሳቢነት ንጉሡ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃዎች ሁሉ ላይ ገዢዎች አድርጎ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን ከንጉሡ አደባባይ ሳይለይ ኖረ።