ዳንኤል 2:24-49
ዳንኤል 2:24-49 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳንኤልም የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ንጉሡ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ሄዶ፣ “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ወደ ንጉሡ ውሰደኝ፤ እኔም ሕልሙን እተረጕምለታለሁ” አለው። አርዮክም ዳንኤልን ወዲያውኑ ወደ ንጉሡ በመውሰድ፣ “ሕልሙንና ትርጕሙን ለንጉሡ መግለጥ የሚችል ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አግኝቻለሁ” አለው። ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን፣ “ያየሁትን ሕልምና ትርጕሙን ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው። ዳንኤልም እንዲህ አለ፤ “አንድም ጠቢብ፣ አስማተኛ፣ ጠንቋይም ሆነ ቃላተኛ ንጉሡ የጠየቀውን ምስጢር መግለጥ የሚችል የለም፤ ነገር ግን ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም በሚመጡት ዘመናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነፆር ገልጧል፤ በዐልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ በአእምሮህ የነበረው ሕልምና ራእይ ይህ ነው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ተኝተህ ሳለ፣ አእምሮህ ወደ ፊት ሊሆን ስላለው ነገር ያሰላስል ነበር፤ ምስጢርን ገላጭ የሆነውም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አሳየህ። ይህ ምስጢር ለእኔ የተገለጠው፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ታላቅ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ትርጕሙን እንድታውቅና በአእምሮህ ታሰላስለው የነበረው ነገር ምን እንደ ሆነ ትረዳ ዘንድ ነው። “ንጉሥ ሆይ፤ በፊት ለፊትህ ግዙፍ የሆነ፣ የሚያብረቀርቅና የሚያስፈራ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ፤ የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤ ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም። ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ። “ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጕሙን ለንጉሥ እንናገራለን። ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤ የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። “ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ቀጥሎም በናስ የተመሰለው ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ መላውን ምድርም ይገዛል። በመጨረሻም ሁሉን ነገር እንደሚቀጠቅጥና እንደሚሰብር ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ሰባብሮ እንደሚያደቅ ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቅቃቸዋል። እግሮቹና ጣቶቹ ከፊል ብረትና ከፊል ሸክላ ሆነው እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ነገር ግን ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ በከፊል የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል። የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት ከፊሉ ሸክላ እንደ ሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ ይሆናል። ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ ብረትና ሸክላ እንደማይዋሃድ ሁሉ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም። “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና ብረቱን፣ ናሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ያደቀቀው ድንጋይ ራእይ ትርጓሜ ይህ ነው፤ “ታላቁ አምላክ ወደ ፊት የሚሆነውን ለንጉሡ አሳይቶታል፤ ሕልሙ እውነት ነው፤ ትርጓሜውም የታመነ ነው።” ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነፆር በግንባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፤ አከበረውም፤ መሥዋዕትና ዕጣንም እንዲያቀርቡለት አዘዘ። ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ይህን ምስጢር ልትገልጥ ችለሃልና፣ በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ፣ ምስጢርንም ገላጭ ነው” አለው። ንጉሡም ዳንኤልን በከፍተኛ ሥልጣን ላይ አስቀመጠው፤ እጅግ ብዙ ስጦታዎችንም ሰጠው፤ የመላው ባቢሎን አውራጃ ገዥ አደረገው፤ በባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ላይም አለቃ አድርጎ ሾመው። ከዚህም በላይ በዳንኤል አሳሳቢነት ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን የባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በቤተ መንግሥት ተቀመጠ።
ዳንኤል 2:24-49 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በኋላ ዳንኤል ንጉሡ የባቢሎን ጠቢባን ያጠፋ ዘንድ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ገባ፥ በገባም ጊዜ፦ የባቢሎንን ጠቢባን አታጥፋ፥ ወደ ንጉሡ አስገባኝ፥ እኔም ፍቺውን ለንጉሡ አሳያለሁ አለው። የዚያን ጊዜም አርዮክ ዳንኤልን ፈጥኖ ወደ ንጉሡ አስገባውና፦ ከይሁዳ ምርኮኞች ያለውን ለንጉሡ ፍቺውን የሚያስታውቀውን ሰው አግኝቼአለሁ አለው። ንጉሡም መለሰ ብልጣሶርም የሚባለውን ዳንኤልን፦ ያየሁትን ሕልምና ፍቺውን ታስታውቀኝ ዘንድ ትችላለህን? አለው። ዳንኤልም በንጉሡ ፊት መልሶ እንዲህ አለ፦ ንጉሡ የጠየቀውን ምሥጢር ጠቢባንና አስማተኞች የሕልም ተርጓሚዎችና ቃላተኞች ለንጉሡ ያሳዩ ዘንድ አይችሉም፥ ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፥ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናብከደነፆር አስታውቆታል። በአልጋህ ላይ የሆነውን ሕልምና የራስህ ራእይ ይህ ነው። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ የሚሆነው ምን እንደ ሆነ በአልጋህ ላይ ታስብ ነበር፥ ምሥጢርንም የሚገልጠው የሚሆነውን ነገር አስታውቆሃል። ነገር ግን ይህ ምሥጢር ለእኔ መገለጡ ፍቺው ለንጉሡ ይታወቅ ዘንድ፥ አንተም የልብህን አሳብ ታውቅ ዘንድ ነው እንጂ በዚህ ዓለም ካሉ ሰዎች ይልቅ በጥበብ ስለ በለጥሁ አይደለም። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ታላቅ ምስል አየህ፥ ይህም ምስል ታላቅና ብልጭልጭታው የበዛ ነበረ፥ በፊትህም ቆሞ ነበር፥ መልኩም ግሩም ነበረ። የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፥ ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ። እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፥ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፥ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ። ሕልሙ ይህ ነው፥ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፥ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፥ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል አንተ የወርቁ ራስ ነህ። ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፥ ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት ይነሣል። አራተኛውም መንግሥት ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፥ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል። እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት ሆኖ እንዳየህ፥ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፥ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ፥ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል። የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁም መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ይሆናል። ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፥ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፥ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም። በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፥ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፥ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች። ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል፥ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው። የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፥ የእህሉንም ቁርባን ዕጣኑንም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ። ንጉሡም ዳንኤልን፦ ይህን ምሥጢር ትገልጥ ዘንድ ተችሎሃልና በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው ብሎ ተናገረው። ንጉሡም ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደርገው፥ ብዙም ታላቅ ስጦታ ሰጠው፥ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ ላይ ሾመው፥ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አለቃ አደረገው። ዳንኤልም ንጉሡን ለመነ፥ እርሱም ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎምን በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ ሾማቸው፥ ዳንኤል ግን በንጉሡ በር ነበረ።
ዳንኤል 2:24-49 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ከንጉሡ ትእዛዝ ወደተሰጠው ወደ አርዮክ ሄደና “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ይልቅስ ወደ ንጉሡ አቅርበኝና የሕልሙን ትርጒም ልንገረው” አለው። አርዮክ ወዲያውኑ ዳንኤልን ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር ፊት አቀረበውና፥ “ንጉሥ ሆይ! የሕልምህን ትርጒም የሚነግርህ ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አንድ ሰው አግኝቼአለሁ” ሲል ለንጉሡ ተናገረ። ንጉሡም ብልጣሶር ተብሎ የሚጠራውን ዳንኤልን “ያየሁትን ሕልም ከነትርጒሙ ልትነግረኝ ትችላለህን?” ሲል ጠየቀው። ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! አንተ የጠየቅኸውን ምሥጢር ጠቢባንም ሆኑ አስማተኞች፤ ጠንቋዮችም ሆኑ መተተኞች ሊነግሩህ አይችሉም። ነገር ግን ምሥጢርን ሁሉ የሚገልጥ አንድ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ ለአንተ ገልጦልሃል፤ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ያየኸው ሕልምና በአእምሮህ የነበረው ራእይ የሚከተለው ነው። “ንጉሥ ሆይ! አንተ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ታሰላስል ነበር፤ ስለዚህ ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስታወቀህ። ይህም ምሥጢር ለእኔ የተገለጠልኝ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ጥበበኛ ስለ ሆንኩ አይደለም፤ ነገር ግን አንተ የሕልሙን ትርጒም እንድታውቅና በአእምሮህም ውስጥ የተመላለሰውን ሐሳብ መረዳት እንድትችል ነው። “ንጉሥ ሆይ! እጅግ የሚያንጸባርቅና ብልጭልጭታው ለማየት የሚያስፈራ ታላቅ ምስል በፊትህ ቆሞ አየህ። የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፥ ደረቱና እጆቹ ከብር፥ ሆዱና ጭኖቹ ከነሐስ፤ ቅልጥሞቹ ከብረት፥ እግሮቹ እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። አንተ ምስሉን ስትመለከት ሳለ ታላቅ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት በምስሉ እግሮች ላይ ወድቆ ሰባበራቸው። ብረቱ፥ ሸክላው፥ ነሐሱ፥ ብሩና ወርቁ ሁሉ ወዲያውኑ ተንከታክቶ በበጋ ወራት በአውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅ ሆነ፤ ምንም ሳያስቀር ነፋስ ጠራርጎ ወሰደው፤ በምስሉ ላይ የወደቀው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ከፍ ከፍ ብሎ ታላቅ ተራራ ሆነ። “እነሆ፥ ሕልሙ ይህ ነው፤ ትርጒሙም እንደሚከተለው ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ከሁሉ የምትበልጥ ንጉሠ ነገሥት ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኀይልን፤ ሥልጣንና ክብርን ሰጥቶሃል። በምድር ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎሃል፤ በሰው፥ በእንስሶችና በወፎች ላይ ሥልጣን ሰጥቶሃል፤ ስለዚህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። ከአንተ በኋላ በገናናነቱ የአንተን መንግሥት የሚያኽል አነስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ከእርሱም ቀጥሎ ዓለምን ሁሉ የሚገዛ በነሐስ የሚመሰል መንግሥት በሦስተኛ ደረጃ ይነሣል። እንደገናም ሁሉን ነገር የሚሰባብርና የሚያንከታክት እንደ ብረት የጠነከረ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ነገር ሰባብሮ እንደሚያደቅ፥ እርሱም ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቃል። እግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ መሆኑን አይተሃል፤ ይህም የሚያመለክተው ያ መንግሥት የተከፋፈለ መሆኑን ነው፤ ብረት ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ ያ መንግሥት በከፊል እንደ ብረት የጠነከረ ይሆናል። የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ብረት፥ እኩሌታው ሸክላ እንደ ሆነ እንዲሁም ያም መንግሥት በከፊል ብርቱ፥ በከፊል ደካማ ይሆናል። ብረቱ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ የእነዚያ የሁለት መንግሥታት ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በመጋባት ይደባለቃሉ፤ ሆኖም ብረት ከሸክላ መዋሐድ እንደማይችል እነርሱም አንድ መሆን አይችሉም፤ በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ግዛቱም በሌላ ሕዝብ የማይደፈር መንግሥትን ይመሠርታል፤ ይህ መንግሥት ሌሎችን መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ላይ ተፈንቅሎ በመውረድ ከብረት፥ ከነሐስ፥ ከሸክላ፥ ከብርና ከወርቅ የተሠራውን ምስል ያደቀቀውም ድንጋይ፥ ያ መንግሥት ነው፤ በዚህም ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አሳይቶሃል፤ እነሆ፥ ሕልሙ እውነት ነው፤ አስተማማኝ ትርጒሙም ይኸው ነው።” ከዚህ በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር ግንባሩ መሬት እስኪነካ ድረስ ወድቆ ለዳንኤል ሰገደለት፤ የእህል ቊርባንና ዕጣን እንዲያቀርቡለትም አዘዘ። ንጉሡም ዳንኤልን “የአንተ አምላክ ከአማልክት ሁሉ የሚበልጥ አምላክ ነው፤ የነገሥታት ሁሉ ጌታ ነው፥ ምሥጢርንም ሁሉ መግለጥ የሚችል ነው፤ ከዚህም የተነሣ ይህን ታላቅ ምሥጢር ለመግለጥ ችለሃል” አለው። ከዚህ በኋላ ንጉሡ ዳንኤልን በታላቅ ክብር ቦታ አስቀመጠው፤ ብዙ ስጦታዎችንም ሰጠው፤ በባቢሎን ግዛትም ሁሉ ላይ የበላይ ገዢ አደረገው፤ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። በዳንኤልም አሳሳቢነት ንጉሡ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃዎች ሁሉ ላይ ገዢዎች አድርጎ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን ከንጉሡ አደባባይ ሳይለይ ኖረ።