ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አየ፤ በጣምም ስለ ተጨነቀ እንቅልፍ አጣ። ስለዚህ ወደ እርሱ መጥተው ያየውን ሕልም ይነግሩት ዘንድ ጠንቋዮች፥ አስማተኞች፥ መተተኞችና የከለዳውያን ኮከብ ቈጣሪዎች እንዲጠሩ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነርሱም መጥተው በፊቱ ቆሙ፤ ንጉሡም “ሕልም አይቼ ስለ ነበር ያ ሕልም ምን እንደ ሆነ እስካውቀው ድረስ እጅግ ተጨንቄአለሁ” አላቸው። እነርሱም “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር! ሕልምህ ምን እንደ ሆነ ንገረንና ትርጒሙን እናስረዳሃለን” ሲሉ በሶርያ ቋንቋ መለሱለት። ንጉሡም እንዲህ አላቸው፦ “መጀመሪያ ሕልሜን፥ ቀጥሎም ትርጒሙን ንገሩኝ፤ አለበለዚያ ግን እጅና እግራችሁ እንዲቈራረጥና ቤታችሁ የፍርስራሽ ክምር እንዲሆን ወስኛለሁ። ሕልሙን ከነትርጒሙ ልትነግሩኝ ብትችሉ ግን ሽልማትና ስጦታ ከታላቅ ክብር ጋር እንድታገኙ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ ሕልሙን ከነትርጒሙ ንገሩኝ።” እነርሱም እንደገና “ንጉሥ ሆይ! ሕልምህ ምን እንደ ሆነ ለእኛ ለአገልጋዮችህ ንገረንና እኛም ትርጒሙን እንንገርህ” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የወሰንኩትን ጥብቅ ውሳኔ ስላወቃችሁ የእናንተ ዕቅድ ነገሩን ለማዘግየት መሆኑን ተረድቼአለሁ፤ ሕልሙን ልትነግሩኝ ባትችሉ ለሁላችሁም አንድ ዐይነት ቅጣት ተዘጋጅቶአል፤ ሁኔታዎች የሚለወጡ መስሎአችሁ የሐሰትና የተንኰል ቃል በመናገር ጊዜ ማራዘም ፈልጋችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ብትነግሩኝ ፍቹም እንደማያስቸግራችሁ ዐውቃለሁ።” የከለዳውያን ኮከብ ቈጣሪዎቹም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “ንጉሥ ሆይ! አንተ ለማወቅ የምትፈልገውን ነገር ሊነግርህ የሚችል ሰው በዓለም ላይ አይገኝም፤ አንድ ንጉሥ የቱንም ያኽል ታላቅና ብርቱ ቢሆን ይህን የመሰለ ጥያቄ ለጠንቋዮች፥ ለአስማተኞችና ለኮከብ ቈጣሪዎች አቅርቦ አያውቅም። ንጉሥ ሆይ! አንተ ለምታቀርበው ከባድ ጥያቄ ከአማልክት በቀር መልስ መስጠት የሚችል የለም፤ አማልክት ደግሞ በሰው መካከል የሚኖሩ አይደሉም።” በዚህን ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቈጥቶ በባቢሎን የሚኖሩ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉ አዘዘ። ጠቢባን እንዲገደሉ በወጣው ትእዛዝ መሠረት ዳንኤልንና ጓደኞቹንም አብረው ለመግደል ፈለጉአቸው። ውሳኔውን በሥራ ላይ እንዲያውል የተመደበው አርዮክ የተባለው የንጉሡ የክብር ዘብ አዛዥ ነበር፤ ስለዚህ ዳንኤል ወደ እርሱ ሄደና በዘዴ አነጋገር፦ “ንጉሡ ይህን ከባድ ውሳኔ ያስተላለፈው እንዴት ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ አርዮክም ጉዳዩን ለዳንኤል ገልጦ አስረዳው። ዳንኤልም ወዲያውኑ ገብቶ ሕልሙን ለመተርጐም ጥቂት ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ለመነ።
ትንቢተ ዳንኤል 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዳንኤል 2:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos