ስለዚህ በእናንተ የሚገኙትን የምድራዊ ሕይወት ምኞቶች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም “ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ፍትወት፥ ክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ የሆነ መጐምጀት” ናቸው። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት በማይታዘዙ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል። እናንተም ራሳችሁ ከዚህ በፊት በማይታዘዙ ሰዎች መካከል ሳላችሁ እነዚህን ነገሮች በማድረግ ትኖሩ ነበር። አሁን ግን ቊጣን፥ ንዴትን፥ ተንኰልን፥ ስም ማጥፋትን ከእናንተ አስወግዱ፤ የሚያሳፍር ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ። አሮጌውን ባሕርይ ከነሥራው አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁት እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። በፈጣሪው አምሳል በዕውቀት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ባሕርይ ልበሱ። በዚህ ሁኔታ በግሪካዊና በአይሁዳዊ፥ በተገረዘና ባልተገረዘ፥ በሠለጠነ አረመኔና ባልሠለጠነ አረመኔ፥ ነጻነት በሌለውና ነጻነት ባለው ሰው መካከል ልዩነት የለም፤ ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የእግዚአብሔር ምርጦችና ቅዱሳን፥ የተወደዳችሁም እንደ መሆናችሁ መጠን ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ ገርነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ይቅር በሉ። ከዚህም ሁሉ በላይ ሁሉን ነገር ሰብስቦ በማሰር ፍጹም አንድነትን የሚያስገኘውን ፍቅርን ልበሱ። የአንድ አካል ክፍሎች ሆናችሁ በእርግጥ የተጠራችሁት ለዚህ ሰላም ስለ ሆነ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት በልባችሁ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊ ዜማም እግዚአብሔርን ከልብ እያመሰገናችሁ ዘምሩ። በኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር አብን እያመሰገናችሁ በቃልም ሆነ በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት፤ በእርሱም እግዚአብሔር አብን አመስግኑ።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3:5-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos