ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:1-20

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:1-20 አማ05

በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥ በቈላስይስ ለሚኖሩ፥ በክርስቶስ ቅዱሳንና ታማኞች ለሆኑ አማኞች፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጸጋና ሰላም ይሁንላችሁ። ለእናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ዘወትር እናመሰግናለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን እምነትና ስለ ምእመናን ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ሰምተናል። የእውነት ቃል የሆነው ወንጌል በመጀመሪያ ወደ እናንተ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ያለውን ተስፋ ሰምታችኋል፤ ስለዚህ እምነታችሁና ፍቅራችሁ የተመሠረተው በሰማይ ተዘጋጅቶ በሚቈያችሁ በዚህ ተስፋ ላይ ነው። እናንተ ወንጌልን ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርንም ጸጋ እውነተኛነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ ይህ ወንጌል በእናንተ መካከል እንደሆነው በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው። ይህንንም በእኛ ምትክ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነውና ከእኛም ጋር አብሮን የሚሠራው የተወደደው ኤጳፍራ ነግሮአችኋል። እንዲሁም እርሱ በእግዚአብሔር መንፈስ እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ነግሮናል። ስለዚህ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እናንተ በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ከመጸለይና እግዚአብሔርን ከመለመን አላቋረጥንም። እንዲሁም ለጌታ ተገቢ በሆነ መንገድ በመኖር እርሱን በፍጹም እንድታስደስቱ ማናቸውንም መልካም ሥራ በመሥራት ፍሬ እንድታፈሩና እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ እንድትሄዱ እንጸልያለን። ጌታ በገናናው ኀይሉ ብርታቱን ሁሉ ይስጣችሁ፤ በትዕግሥትም ሁሉን ነገር ለመቻል በደስታ የተዘጋጃችሁ ለመሆን ያብቃችሁ፤ ደግሞም በብርሃን መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድትካፈሉ ያበቃችሁን እግዚአብሔር አብን በደስታ አመስግኑት። እርሱ ከጨለማ ኀይል አድኖ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል። በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አግኝተናል። ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ በላይ ታላቅና በኲር ነው። በሰማይና በምድር ያሉት፥ የሚታዩትና የማይታዩት፥ የሰማይ ኀይሎችና ገዢዎች፥ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። እርሱ ከሁሉ ነገር በፊት ነበረ፤ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር ቀዳሚ እንዲሆን፤ ከሞት በመነሣትም ፊተኛና መጀመሪያ ነው። ይህም የሆነው የመለኮት ሙላት በልጁ እንዲኖር የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ስለ ሆነ ነው። በእርሱም አማካይነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ፤ በመስቀል ላይ በፈሰሰው በልጁ ደምም ሰላምን አደረገ።