ትንቢተ አሞጽ 5:1-27

ትንቢተ አሞጽ 5:1-27 አማ05

የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእናንተ ላይ እኔ የማወርደውን ይህን ሙሾ አድምጡ፦ እነሆ ድንግሊቱ እስራኤል ወደቀች፤ እንደገናም መነሣት አትችልም የሚያነሣት ረዳት በማጣት በገዛ ምድርዋ የተተወች ብቸኛ ሆነች። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከአንዲት የእስራኤል ከተማ ሺህ ጦረኞች ይዘምታሉ፤ በሕይወት የሚቀሩት ግን አንድ መቶ ብቻ ይሆናሉ፤ ከሌላይቱም ከተማ መቶ ጦረኞች ይዘምታሉ፤ ተመልሰው የሚመጡት ግን ዐሥር ብቻ ይሆናሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደ እኔ ተመለሱ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ወደ ቤርሳቤህ አትሂዱ፤ ቤቴል ፈራርሳ እንዳልነበረች ስለምትሆን በጌልገላ የሚኖሩ ሕዝቦችም ስደት ስለ ተፈረደባቸው ወደ ቤቴልም ሆነ ወደ ጌልጌላ አትሂዱ።” ይልቅስ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ አለበለዚያ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እንደ እሳት ሆኖ ያጋያቸዋል፤ የቤትኤልንም ኗሪዎች እሳት ይበላቸዋል፤ እሳቱን የሚያጠፋላቸውም አይገኝም። እናንተ ፍርድን የምታጣምሙና እውነትን ወደ ሐሰት የምትለውጡ ወዮላችሁ! “ፕሊያዲስ” የተባሉትን ሰባቱን ከዋክብትና “ኦርዮን” ተብለው የሚጠሩትን የከዋክብት ክምችትን የፈጠረ፥ ሌሊቱን ወደ ቀን፥ ቀኑንም ወደ ሌሊት የሚለውጥ፥ የባሕሩን ውሃ አዞ፥ በምድር ላይ እንዲፈስ የሚያደርግ፥ ኀያላንንና ምሽጎቻቸውን የሚደመስስ እርሱ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው። እናንተ በፍርድ አደባባይ የሚገሥጻችሁን ጠላችሁ፤ እውነት የሚናገረውንም ተጸየፋችሁ። ድኾችን ጨቊናችሁ፤ እህላቸውንም አስገብራችሁ፤ ከጥርብ ድንጋይ ቤቶች ሠርታችኋል፤ እናንተ ግን አትኖሩባቸውም፤ የሚያስደስት ወይን ተክላችኋል፤ ነገር ግን ከእርሱ የሚገኘውን የወይን ጠጅ እናንተ አትጠጡም። በደላችሁ ምን ያኽል እንደ በዛና ኃጢአታችሁም ምን ያኽል ከባድ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ደጋግ ሰዎችን ታስጨንቃላችሁ፤ ጉቦ እየተቀበላችሁ በየፍርድ አደባባዩ የምስኪኖችን ፍትሕ ታጣምማላችሁ። ስለዚህ ዘመኑ ክፉ ስለ ሆነ አስተዋይ የሆነ ሰው ዝም ይላል። በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉ ነገር አታድርጉ፤ ይህን ብታደርጉ ልክ እናንተ እንደምትሉት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል። ክፉውን ነገር ጥሉ፤ መልካም የሆነውን ነገር ውደዱ፤ በየፍርድ አደባባዩም ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለተረፉት የእስራኤል ሕዝብ ምሕረት ያደርግላቸው ይሆናል። ስለዚህ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በየመንገዱና በየአደባባዩ ዋይታና ለቅሶ ይሰማል፤ ገበሬዎች እንኳ ለለቅሶ ይጠራሉ፤ ከሙሾ አውጪዎችም ጋር ስለ ሞቱ ሰዎች ያለቅሳሉ፤ በወይን ተክል ቦታዎች ሁሉ ለቅሶ ይሆናል፤ ይህም ሁሉ የሚሆነው እኔ በመካከላችሁ ስለማልፍ ነው፤” ይህንንም የተናገረ እግዚአብሔር ነው። እናንተ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት የምትጠባበቁ ወዮላችሁ! ያ ቀን የጨለማ እንጂ የብርሃን ቀን ስላይደለ ለምን ያንን ቀን ትጠባበቃላችሁ? ያ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሸሽቶ ሲሄድ ድብ እንደሚያጋጥመው፥ ወይም አምልጦ ወደ ቤቱ ሲገባ እጁን በግድግዳ ላይ ቢያሳርፍ እባብ እንደሚነድፈው ሁኔታ ይሆንባችኋል። በእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ጨለማ እንጂ ብርሃን አይሆንላችሁም፤ ያ ቀን ምንም ብርሃን የማይታይበት ድቅድቅ ጨለማ ይሆንባችኋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዓመት በዓሎቻችሁን ሁሉ እጠላለሁ፤ እንቃለሁም፤ የአምልኮ ስብሰባዎቻችሁም አያስደስቱኝም። የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል መባ ብታቀርቡልኝ እንኳ አልቀበላችሁም፤ ለደኅንነት መሥዋዕት ወደምታቀርቡልኝ የሰቡ ፍሪዳዎችም አልመለከትም። የመዝሙራችሁን ጩኸት ከእኔ አርቁ፤ የበገናችሁንም ዜማ መስማት አልፈልግም፤ ይልቅስ ፍትሕ እንደ ወራጅ ውሃ፥ ጽድቅም እንደማያቋርጥ የወንዝ ውሃ ይፍሰስ። “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በውኑ በአርባው ዓመት የምድረ በዳው ጒዞ ጊዜ መሥዋዕትና መባ አቅርባችሁልኛልን? ለራሳችሁ የሠራችኋቸውን ‘ንጉሥ የምትሉትን’ ሳኩት የተባለውን ጣዖታችሁን፥ እንዲሁም ‘ኬዋን’ የተባለውን የኮከብ ጣዖታችሁን ትሸከማላችሁ። ከደማስቆ ወዲያ ርቃችሁ እንድትሰደዱ አደርጋለሁ።” ይህን የተናገርኩ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነኝ።