ትንቢተ አሞጽ 1
1
1ዖዝያን በይሁዳ፥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓምም በእስራኤል ላይ በነገሡበት ዘመን፥ በተቆዓ ከሚገኙ እረኞች አንዱ የሆነው አሞጽ የምድር መናወጥ ከመሆኑ ሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል የተናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው። #2ነገ. 15፥1-7፤ 2ዜ.መ. 26፥1-23፤ 2ነገ. 14፥23-29።
2አሞጽ እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ሆኖ
እንደሚያገሣ አንበሳ
የሚያስፈራ ድምፁን ያሰማል፤
ቃሉም ከኢየሩሳሌም ያስተጋባል፤
እረኞች መንጋ የሚያሰማሩበት መስክ ይጠወልጋል፤
በቀርሜሎስ ተራራ የሚገኘውም ልምላሜ ይደርቃል።” #ኢዩ. 3፥16።
የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ጐረቤት አገሮች ላይ
ሶርያ
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የደማስቆ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የገለዓድን ሕዝብ የብረት ጥርስ ባለው መንኰራኲር አበራይተው አሠቃይተዋቸዋል። #ኢሳ. 17፥1-3፤ ኤር. 49፥23-27፤ ዘካ. 9፥1። 4በንጉሥ ሐዛኤል ቤተ መንግሥት ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ እሳቱም ንጉሥ ቤንሀዳድ የሠራቸውንም ምሽጎች ያቃጥላል። 5የደማስቆን ከተማ የቅጽር በር መዝጊያ ሁሉ እሰባብራለሁ፤ በአዌን ሸለቆ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የቤትዔደንን መሪ አስወግዳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይወሰዳሉ።”
ፍልስጥኤም
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የጋዛ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የሀገሩን ሕዝብ ሁሉ ከማረኩ በኋላ ለኤዶም ሰዎች አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። #ኢሳ. 14፥29-31፤ ኤር. 47፥1-7፤ ሕዝ. 25፥15-17፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ ሶፎ. 2፥4-7፤ ዘካ. 9፥5-7። 7ስለዚህ በጋዛ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል፤ 8በአሽዶድ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የአስቀሎናን መሪ አጠፋለሁ፤ የዔቅሮን ከተማ ኗሪዎችንም እቀጣለሁ፤ የተረፉትም ፍልስጥኤማውያን ይሞታሉ።”
ጢሮስ
9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የጢሮስ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ የገቡበትን የወንድምነት ቃል ኪዳን አፍርሰው የማረኳቸውን ሕዝቦች ለኤዶም አሳልፈው ሰጥተዋል፤ 10ስለዚህ በጢሮስ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል።” #ኢሳ. 23፥1-8፤ ሕዝ. 26፥1—28፥19፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ ዘካ. 9፥1-4፤ ማቴ. 11፥21-22፤ ሉቃ. 10፥13-14።
ኤዶም
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የኤዶም ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ወንድሞቻቸውን እስራኤላውያንን በሰይፍ አሳደዋቸዋል፤ ከያዙአቸውም በኋላ ርኅራኄ አላደረጉላቸውም፤ በእነርሱ ላይ ያላቸው ቊጣ ሊበርድም አልቻለም፤ #ኢሳ. 34፥5-17፤ 63፥1-6፤ ኤር. 49፥7-22፤ ሕዝ. 25፥12-14፤ 35፥1-15፤ አብ. 14፤ ሚል. 1፥2-5። 12ስለዚህ በቴማን ከተማ ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ የቦጽራንም ምሽጎች ያቃጥላል።”
ዐሞን
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዐሞን ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ግዛት ለማስፋፋት ባደረጉት ወረራ በገለዓድ የሚኖሩትን እርጉዞች ሴቶች እንኳ ሆዳቸውን ቀደዋል። #ኤር. 49፥1-6፤ ሕዝ. 21፥28-32፤ 25፥1-7፤ ሶፎ. 2፥8-11። 14ስለዚህ በራባ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል፤ ከዚህ በኋላ በጦርነቱ ቀን ጩኸትና ሁካታ ይበዛል፤ ጦርነቱም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይፈጥናል፤ 15ንጉሣቸውና መሳፍንቱ ተማርከው ይሄዳሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 1: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997