ጴጥሮስ በየአገሩ ሲዘዋወር ሳለ በልዳ ወደሚኖሩት ምእመናን ሄደ። እዚያም ስምንት ዓመቶች ሙሉ በአልጋ ላይ የተኛ ኤኒያ የሚባለውን ሽባ አገኘ። ጴጥሮስም “ኤኒያ ሆይ! ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሥና አልጋህን አንጥፍ!” አለው፤ እርሱም ወዲያውኑ ተነሣ። የልዳና የሳሮናም ነዋሪዎች ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ተመለሱ። በኢዮጴም ጣቢታ የምትባል አንዲት አማኝ ነበረች፤ የስሟም ትርጒም በግሪክኛ ዶርቃ ትርጒሙም ሚዳቋ ማለት ነው፤ እርስዋ መልካም ነገር ማድረግና ለድኾች መለገሥ የምታዘወትር ሴት ነበረች፤ በዚያን ጊዜ እርስዋ ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት ላይ ባለው ክፍል ውስጥ አኖርዋት። ልዳ ለኢዮጴ ቅርብ ስለ ነበረች በኢዮጴ ያሉት ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በልዳ መኖሩን ሰምተው “እባክህን ሳትዘገይ በቶሎ ድረስልን” ብለው ሁለት ሰዎች ላኩበት። ስለዚህ ጴጥሮስ ተነሥቶ ከመልእክተኞቹ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነቱ ላይ ወዳለው ክፍል ወሰዱት፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ሁሉ በዙሪያው ቆመው እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር በሕይወት ሳለች የሠራቻቸውን ቀሚሶችና ልብሶች ያሳዩት ነበር፤ ጴጥሮስ ግን ሁሉንም ወደ ውጪ አስወጣና ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ አስከሬኑም መለስ አለና “ጣቢታ! ተነሺ!” አለ፤ እርስዋም ዐይኖችዋን ከፈተች፤ ጴጥሮስንም አየች፤ ተነሥታም ቁጭ አለች። እርሱም እጁን ዘርግቶ ያዘና አስነሣት፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ሌሎችንም አማኞች ጠርቶ ልጅቷን በሕይወት በፊታቸው አቀረባት። ይህም ነገር በኢዮጴ ሁሉ ታወቀ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። ጴጥሮስም ስምዖን ከሚባለው አንድ ቊርበት ፋቂ ጋር ለብዙ ቀኖች በኢዮጴ ተቀመጠ።
የሐዋርያት ሥራ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 9:32-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች