የጌታ መልአክ ፊልጶስን፥ “ተነሥና ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ወደ ደቡብ ሂድ” አለው፤ ያ መንገድ የበረሓ መንገድ ነበር። እርሱም ተነሥቶ ሄደ፤ እነሆ፥ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ለእግዚአብሔር ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር፤ ይህ ሰው ሕንደኬ ለተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ባለሟልና የገንዘብዋ ሁሉ ኀላፊ ነበረ። እርሱ ወደ አገሩ ሲመለስ በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን “ሂድ ወደዚያ ሠረገላ ቅረብና ተገናኘው” አለው። ስለዚህ ፊልጶስ ወደዚያ ሮጦ ሄደና ኢትዮጵያዊው የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ “የምታነበው ትርጒሙ ይገባሃልን?” አለው። ኢትዮጵያዊውም “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ሊገባኝ ይችላል?” አለና ፊልጶስን “ወደ ሠረገላው ውጣና ከእኔ ጋር ተቀመጥ” አለው። እርሱም ያነበው የነበረው የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል የሚከተለው ነበረ፦ “እርሱ ለመታረድ እንደሚነዳ በግ ነበረ፤ ሲሸልቱትም ዝም እንደሚል ጠቦት፤ እርሱም ለመናገር አፉን አልከፈተም። እርሱ ተዋረደ፤ ቅን ፍርድም አልተሰጠውም፤ ሕይወቱም ከምድር ተወግዶአልና ስለ ትውልዱ ማን ሊናገር ይችላል?” ጃንደረባውም ፊልጶስን፥ “ነቢዩ ይህን የተናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ? እባክህን ንገረኝ” አለው። ፊልጶስም ከዚህ የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ መልካሙን ዜና አበሠረው። ሲሄዱም ውሃ ወዳለበት ቦታ ደረሱ፤ ጃንደረባውም “እነሆ፥ እዚህ ውሃ አለ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ነገር ምንድን ነው?” አለ። [ ፊልጶስም “በሙሉ ልብህ ካመንክ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ” አለ።] ጃንደረባው ሠረገላው እንዲቆም አዘዘ፤ ሁለቱም ወደ ውሃው ወረዱና ፊልጶስ ጃንደረባውን አጠመቀው። ከውሃው ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ወሰደው፤ ጃንደረባውም ዳግመኛ አላየውም፤ ይሁን እንጂ ደስ እያለው ጒዞውን ቀጠለ።
የሐዋርያት ሥራ 8 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 8:26-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos