የሐዋርያት ሥራ 3:1-8

የሐዋርያት ሥራ 3:1-8 አማ05

አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፤ እዚያ “ውብ” እየተባለ የሚጠራ በር ነበር፤ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የሆነውን አንድ ሰው ሰዎች በየቀኑ እያመጡ እዚያ ያስቀምጡት ነበር፤ እርሱ እዚያ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት ይለምን ነበር። ይህ ሰው ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው። እነርሱም ሰውየውን ትኲር ብለው አዩትና ጴጥሮስ “ወደ እኛ ተመልከት!” አለው። እርሱም ምጽዋት የሚሰጡት መስሎት ትኲር ብሎ አያቸው። ጴጥሮስ ግን “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ተራመድ!” አለው። ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውኑ እግሩና ቊርጭምጭሚቱ በረታ። ብድግ ብሎም ቆመ፤ እየተራመደም ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ እየተራመደና እየዘለለም እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር።