ወደ ኢጣሊያ በመርከብ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ ጳውሎስንና ሌሎችንም እስረኞች በአውግስጦስ ክፍለ ጦር ውስጥ ለነበረው ዩልዮስ ለሚባለው መቶ አለቃ አስረከቡአቸው። በእስያ የባሕር ዳርቻ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው የአድራሚጥዮን መርከብ ተሳፍረን ተጓዝን፤ በተሰሎንቄ የሚኖረው የመቄዶንያው ሰው አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋር ነበረ። በማግስቱ ወደ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስ ለጳውሎስ ደግ ስለ ነበረ ወደ ወዳጆቹ ሄዶ የሚያስፈልገውን ርዳታ እንዲያደርጉለት ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ከፊት ለፊት ይነፍስብን ስለ ነበር የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን በመርከብ ጒዞአችንን ቀጠልን። በኪልቅያና በጵንፍልያ አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሊቅያ አገር ወዳለው ወደ ሙራ ከተማ ደረስን። እዚያ የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አገኘና በእርሱ ላይ እንድንሳፈር አደረገ። ብዙ ቀን ቀስ እያልን ተጒዘን በብዙ ችግር ወደ ቀኒዶስ ከተማ አጠገብ ደረስን፤ ነፋሱም ወደፊት እንዳንሄድ ስለ ከለከለን በሰልሞና ርእሰ ምድር ጫፍ አጠገብ አለፍንና የቀርጤስን ደሴት ተገን አድርገን ሄድን። በብዙ ችግር ጥግ ጥጉን ካለፍን በኋላ በላስያ ከተማ አጠገብ ወደምትገኘው “መልካም ወደብ” ወደምትባለው ስፍራ ደረስን። በጒዞአችን ላይ ብዙ ጊዜ በመባከኑና የጾም ጊዜ በማለፉ ምክንያት በዚህ ጊዜ በባሕር ላይ መጓዝ አደገኛ ስለ ነበር ጳውሎስ ለሰዎቹ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው፤ “እናንተ ሰዎች! ከእንግዲህ ወዲህ ያለው ጒዞአችን አደጋ እንዳለበት ይታየኛል፤ በጭነቱና በመርከቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ሕይወትም ላይ ብርቱ ጒዳትና ጥፋት ይደርሳል።” የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ አዛዥና የመርከቡ ባለቤት የሚሉትን ይሰማ ነበር። ያ ወደብ ለክረምት ማሳለፊያ ምቹ ስላልነበረ አብዛኞቹ ሰዎች “ጒዞአቸውን ቀጥለው የሚቻል ቢሆን በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ በር ወዳለው ፊንቄ ወደሚባለው የቀርጤስ ወደብ ደርሰን ክረምቱን እዚያ እናሳልፍ” ብለው አሳብ አቀረቡ።
የሐዋርያት ሥራ 27 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 27:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos