በማግስቱ ሌሊት ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ “አይዞህ በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርክልኝ፥ እንዲሁም በሮም ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” አለው። በነጋ ጊዜ አይሁድ ተሰበሰቡና “ጳውሎስን ሳንገድል እህል አንበላም፤ ውሃም አንጠጣም” ብለው ተማማሉ። በዚህ ሤራ የተስማሙ ሰዎች ቊጥራቸው ከአርባ በላይ ነበር። እነርሱ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ ሲሉ ነገሩአቸው፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል እንዳንቀምስ በጥብቅ ተማምለናል፤ ስለዚህ እናንተ ከሸንጎው ጋር ተስማምታችሁ በጥብቅ የምትመረምሩት ነገር እንዳለ በማስመሰል ጳውሎስን እንዲያመጡላችሁ አዛዡን ጠይቁት፤ እኛም እዚህ ከመድረሱ በፊት ልንገድለው ተዘጋጅተናል።” ነገር ግን የጳውሎስ የእኅት ልጅ ይህን ሤራ ስለ ሰማ ወደ ወታደሮች ሰፈር ሄዶ ገባና ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ “ይህ ልጅ ለጦር አዛዡ የሚናገረው ነገር ስላለው ወደ እርሱ አቅርበው” አለው። የመቶ አለቃውም ልጁን ወደ አዛዡ ይዞ ገባና “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ ይህ ልጅ ለአንተ የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ለመነኝ” አለ። አዛዡም የልጁን እጅ ይዞ ገለል አደረገውና “የምትነግረኝ ነገር ምንድን ነው?” ሲል ለብቻው ጠየቀው። ልጁም እንዲህ አለ፤ “አይሁድ የጳውሎስን ነገር በጥብቅ የሚመረምሩ መስለው ነገ ወደ ሸንጎው እንድታቀርብላቸው ሊጠይቁህ ተስማምተዋል። ነገር ግን እሺ አትበላቸው፤ እርሱን ሳንገድል እህል አንበላም፤ ውሃም አንጠጣም በማለት የተማማሉ ከአርባ የሚበልጡ ሰዎች እርሱን ለመግደል አድፍጠዋል፤ አሁን እነርሱ የሚጠብቁት የአንተን መልስ ብቻ ነው።” አዛዡም “ይህን ነገር ለእኔ መንገርህን ለማንም አትግለጥ” ብሎ ልጁን አሰናበተው። ከዚህ በኋላ የጦር አዛዡ ከመቶ አለቆቹ ሁለቱን ጠርቶ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ሲሆን ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ ሁለት መቶ ወታደሮችና ሰባ ፈረሰኞች፤ ሁለት መቶ ጦር ወርዋሪዎችም አዘጋጁ፤ ለጳውሎስም ፈረስ አዘጋጁለትና ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲደርስ አድርጉት” አላቸው። እንዲህ የሚል ደብዳቤም ጻፈ፤ “ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ፤ ለክቡር አገረ ገዢ ፊልክስ! ሰላም ለአንተ ይሁን! ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ እኔ ግን የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅሁ ከወታደሮች ጋር ደርሼ አዳንኩት። በምን ምክንያት እንደ ከሰሱት ለማወቅ ፈልጌም ወደ ሸንጎአቸው አቅርቤው ነበር። የከሰሱትም ሕጋቸውን በሚመለከት ነገር መሆኑን ተረዳሁ፤ ነገር ግን ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርሰው ነገር የለም። ይህን ሰው ለመግደል ሤራ እንደ ተደረገ በሰማሁ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም በእርሱ ላይ ያላቸውን ክስ በአንተ ፊት እንዲያቀርቡ ነግሬአቸዋለሁ።” ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት ጳውሎስን በሌሊት ወስደው ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት። በማግስቱ ፈረሰኞቹ ከጳውሎስ ጋር ጒዞአቸውን እንዲቀጥሉ አድርገው እነርሱ ወደ ጦር ሰፈሩ ተመለሱ። ፈረሰኞቹ ወደ ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ ደብዳቤውን ለአገረ ገዥው ሰጡና ጳውሎስን በፊቱ አቀረቡት። አገረ ገዥው ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ ጳውሎስን “ከየትኛው ክፍለ ሀገር ነህ?” ሲል ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑን ባወቀ ጊዜ “ከሳሾችህ ሲመጡ ጉዳይህን እሰማለሁ” አለው። በሄሮድስ ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲጠበቅም አዘዘ።
የሐዋርያት ሥራ 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 23:11-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች