በሚቀጥለውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” አለው። በነጋም ጊዜ፣ አይሁድ ተሰብስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ። በዚህ ሤራ የተማማሉትም ከአርባ በላይ ነበሩ። እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ አድርገናል። እንግዲህ እናንተ ከሸንጎው ጋራ ሆናችሁ፣ ስለ ጕዳዩ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ከርሱ እንደምትፈልጉ አስመስላችሁ ጳውሎስን ወደ እናንተ እንዲሰድደው የጦር አዛዡን ለምኑት፤ እኛም ገና ወደዚህ ሳይደርስ ልንገድለው ዝግጁ ነን።” ነገር ግን የጳውሎስ የእኅት ልጅ ስለ ሤራው በመስማቱ፣ ወደ ጦሩ ሰፈር ገብቶ ሁኔታውን ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስም ከመቶ አለቆቹ አንዱን ጠርቶ፣ “ይህ ልጅ ለጦር አዛዡ የሚነግረው ነገር ስላለ ወደ እርሱ ውሰደው” አለው። እርሱም ወደ ጦር አዛዡ ወሰደው። የመቶ አለቃውም፣ “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ፣ ይህ ጕልማሳ የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ለመነኝ” አለው። አዛዡም የጕልማሳውን እጅ ይዞ ለብቻው ገለል በማድረግ፣ “ልትነግረኝ የምትፈልገው ምንድን ነው?” አለው። ልጁም እንዲህ አለው፤ “አይሁድ ስለ እርሱ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የፈለጉ በመምሰል፣ ጳውሎስን ነገ ሸንጎው ፊት እንድታቀርብላቸው ሊለምኑህ ተስማምተዋል። ስለዚህ ዕሺ አትበላቸው፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑት ሊገድሉት አድፍጠው እየጠበቁት ነው፤ ደግሞም እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን መልስ እየተጠባበቁ ነው።” የጦር አዛዡም፣ “ይህን ለእኔ የገለጥህልኝን ነገር ለማንም እንዳትናገር” ብሎ ጕልማሳውን አስጠንቅቆ አሰናበተው። ከዚያም ከመቶ አለቆቹ ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት፣ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ ሁለት መቶ ወታደሮች፣ ሰባ ፈረሰኞችና ሁለት መቶ ባለጦር ጭፍራ አዘጋጁ፤ ደግሞም ጳውሎስ ተቀምጦበት ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ በደኅና የሚደርስበት ከብት ይዘጋጅ።” ደብዳቤም ጻፈ፤ እንዲህ የሚል፦ ከቀላውዴዎስ ሉስያስ፤ ለክቡር አገረ ገዥ ለፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን። አይሁድ ይህን ሰው ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ ነገር ግን የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅሁ፣ ከወታደሮቼ ጋራ ደርሼ አተረፍሁት። ለምን ሊከስሱት እንደ ፈለጉ ለማወቅም ወደ ሸንጓቸው አቀረብሁት። የተከሰሰውም ሕጋቸውን በተመለከተ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ። አይሁድ ግን በዚህ ሰው ላይ ማሤራቸውን በተረዳሁ ጊዜ፣ ወዲያው ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም ከርሱ ጋራ ያላቸውን ክርክር ለአንተ እንዲያቀርቡ አዘዝኋቸው። ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት፣ ጳውሎስን ይዘው በሌሊት እስከ አንቲጳጥሪስ ድረስ ወሰዱት። በማግስቱም፣ ፈረሰኞቹ ብቻ እንዲያደርሱት አድርገው፣ ሌሎቹ ወደ ጦር ሰፈር ተመለሱ። ፈረሰኞቹም ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ፣ ደብዳቤውን ለአገረ ገዥው ሰጡት፤ ጳውሎስንም አስረከቡት። አገረ ገዥውም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ፣ ጳውሎስን ከየትኛው አውራጃ እንደ መጣ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ “የአንተን ጕዳይ ከሳሾችህ ሲቀርቡ አያለሁ” አለው። ከዚያም ጳውሎስ በሄሮድስ ግቢ ውስጥ እንዲጠበቅ አዘዘ።
ሐዋርያት ሥራ 23 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 23
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 23:11-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች