የሐዋርያት ሥራ 23:1-10

የሐዋርያት ሥራ 23:1-10 አማ05

ጳውሎስም ሸንጎውን ትኲር ብሎ ተመለከተና “ወንድሞቼ ሆይ! እስከ ዛሬ ድረስ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የኖርኩት በመልካም ኅሊና ነው” አለ። የካህናት አለቃው ሐናንያ ግን ጳውሎስን አፉን እንዲመቱት በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አዘዘ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ሐናንያን፥ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳን የምትመስል! አንተንም እግዚአብሔር ይመታሃል! በሕግ መሠረት የእኔን ጉዳይ ልትፈርድ ተቀምጠህ ሳለ ያለ ሕግ እንዲመቱኝ ታዛለህን?” እዚያ የነበሩ ሰዎች ጳውሎስን “የእግዚአብሔርን የካህናት አለቃ ትሳደባለህን?” አሉት። ጳውሎስም “ወንድሞቼ ሆይ! የካህናት አለቃ መሆኑን አላወቅሁም ነበር፤ ምክንያቱም ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር’ የሚል ተጽፎአል” አለ። ጳውሎስ እዚያ ከነበሩት ሰዎች እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ዐውቆ “ወንድሞቼ ሆይ! እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ፤ እነሆ! አሁን በፍርድ ፊት የቀረብኩት በተሰጠው ተስፋና በሙታን ትንሣኤ ምክንያት ነው” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ በሸንጎው መካከል ተናገረ። ጳውሎስ ይህን በተናገረ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሥቶ ሸንጎው ለሁለት ተከፈለ። ሰዱቃውያን “ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም የሉም፤ መንፈስም የለም” ሲሉ ፈሪሳውያን ግን “እነዚህ ሁሉ አሉ” ብለው ያምናሉ። በዚህ ጊዜ ታላቅ ሁካታ ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ የሕግ መምህራንም ተነሡና “እኛ በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮት ይሆናል፤ እኛ ምን እናውቃለን?” በማለት ተከራከሩ። ጠቡ እየከረረ ስለ ሄደ ሰዎቹ ጳውሎስን እንዳይቦጫጭቁት ፈርቶ አዛዡ “ውረዱና ጳውሎስን ከሰዎቹ መካከል ነጥቃችሁ አምጡ! ወደ ጦሩ ሰፈርም ውሰዱት!” በማለት ወታደሮቹን አዘዘ።