ሁከቱ ጸጥ ካለ በኋላ ጳውሎስ ምእመናኑን በአንድነት አስጠርቶ በምክር ቃል አጽናናቸው፤ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ሄደ። በእነዚያ በሚያልፍባቸው ስፍራዎች ምእመናንን በብዙ ምክር እያበረታታ ወደ ግሪክ አገር ሄደ። እዚያም ሦስት ወር ቈየ፤ ከዚህ በኋላ በመርከብ ወደ ሶርያ ለመሄድ አሰበ፤ ግን አይሁድ በእርሱ ላይ ሤራ ማድረጋቸውን ባወቀ ጊዜ በመቄዶንያ በኩል ለመመለስ ወሰነ። የጲርሁስ ልጅ ሶጳጥሮስ ከቤርያ፥ አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ ከተሰሎንቄ፥ ጋይዮስ ከደርቤ፥ ጢሞቴዎስ፥ ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ ከእስያ አብረውት ሄዱ። እነርሱ ቀድመውን ሄደው በጢሮአዳ ቈዩን። እኛ ግን ከቂጣ በዓል በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተሳፍረን በአምስት ቀን እነርሱ ወዳሉበት ወደ ጢሮአዳ ደረስንና እዚያ ሰባት ቀን አሳለፍን። ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እንጀራ ቈርሶ በአንድነት ለመብላት ተሰበሰብን፤ ጳውሎስ በማግስቱ መሄድ ስለ ነበረበት ለተሰበሰቡት ሰዎች ይናገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት አስረዘመ። እኛ በተሰበሰብንበት ፎቅ ብዙ መብራት ነበር። ኤውጤኪስ የተባለ አንድ ወጣት በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን በማስረዘሙ ወጣቱ ከባድ እንቅልፍ ያዘው፤ እንቅልፍ ስላሸነፈውም ከሦስተኛው ፎቅ ወደ ታች ወደቀ፤ ሰዎች ባነሡት ጊዜ ሞቶ አገኙት። ነገር ግን ጳውሎስ ወርዶ በልጁ ላይ ጐንበስ በማለት አቀፈውና “ገና በሕይወት አለ፤ አትደንግጡ!” አለ። ጳውሎስ ወደ ፎቅ ተመልሶ ወጣና እንጀራ ቈርሶ ከአማኞች ጋር በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ከቈየ በኋላ ሄደ። ሰዎቹም የዳነውን ወጣት ወደ ቤት ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ። ጳውሎስን ለማሳፈር ስለ አሰብን እኛ ቀድመን በመርከብ ወደ አሶስ ሄድን፤ ይህንንም ያደረግነው ጳውሎስ እስከ አሶስ ድረስ በእግሩ ለመሄድ ስለ ወሰነና እንዲህ እንድናደርግ ስለ አዘዘን ነው። ከእርሱ ጋር በአሶስ በተገናኘን ጊዜ በመርከብ አሳፍረነው ወደ ሚጢሊኒ አብረን ሄድን። በማግስቱ ከዚያ ተነሥተን በኪዮስ ፊት ለፊት ወዳለው ስፍራ በመርከብ ደረስን፤ በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞስ ተሻገርንና በማግስቱ ወደ ሚሊጢ ደረስን። ጳውሎስ በእስያ ጊዜ እንዳያባክን ብሎ ኤፌሶንን አልፎ ለመሄድ ፈለገ፤ ይህንንም ያደረገው ለጰንጠቆስጤ በዓል በኢየሩሳሌም ለመገኘት አስቦ ስለ ነበር ነው። ጳውሎስ ከሚሊጢ ወደ ኤፌሶን ሰው ልኮ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አስጠራ፤ ወደ እርሱ በመጡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ እስያ ከገባሁበት ቀን ጀምሮ ዘወትር ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርኩ እናንተ ታውቃላችሁ፤ በአይሁድ ሤራ ምክንያት መከራ ቢደርስብኝም እንኳ በፍጹም ትሕትናና በእንባ ጌታን አገለግል ነበር። በአደባባይም ሆነ በየቤታችሁ ሳስተምራችሁ የሚጠቅማችሁን ሁሉ ነገርኳችሁ እንጂ፥ ምንም ነገር አላስቀረሁባችሁም። አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ አስጠነቀቅኋቸው። አሁንም እዚያ ስደርስ ምን እንደሚደርስብኝ ሳላውቅ በመንፈስ ቅዱስ ታዝዤ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዴ ነው። ይሁን እንጂ በየከተማው እስራትና ችግር እንደሚገጥመኝ መንፈስ ቅዱስ ነግሮኛል። የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል ለማስተማር ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልኩትን የማገልገል ግዴታ ከፈጸምኩ ለሕይወቴ ዋጋ አልሰጠውም፤ ለነፍሴም አልሳሳለትም። “እስከ አሁን በእናንተ ሁሉ መካከል እየተዘዋወርኩ የእግዚአብሔርን መንግሥት እሰብክ ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከእናንተ ማንም ከቶ ፊቴን እንደማያይ ዐውቃለሁ። ስለዚህ ከእናንተ አንድ እንኳ ቢጠፋ ኀላፊነት እንደሌለብኝ በዛሬው ቀን አስገነዝባችኋለሁ። የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሁሉ ነገርኳችሁ እንጂ ምንም ያስቀረሁባችሁ ነገር የለም። መንፈስ ቅዱስ እናንተን ኤጲስ ቆጶሳት አድርጎ ሾሞአችኋል፤ እንግዲህ ለራሳችሁና ለመንጋው ተጠንቀቁ፤ እግዚአብሔር በገዛ ልጁ ደም የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ። እኔ ከሄድኩ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ እንደ ተኲላ ጨካኞች የሆኑ ሰዎች እንደሚገቡባችሁ ዐውቃለሁ። እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው ጠማማ ትምህርት በማስተማር ብዙ አማኞችን ወደ እነርሱ ይስባሉ። ስለዚህ እያንዳንዳችሁን ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን እንባዬን እያፈሰስኩ እንደ መከርኳችሁ እያስታወሳችሁ ተጠንቀቁ። “አሁንም ሊያንጻችሁና በቅዱሳንም መካከል ርስት ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለእግዚአብሔርና ለጸጋው ቃልም ዐደራ ሰጥቼአለሁ። እኔ የማንንም ብር፥ ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም። በገዛ እጆቼ እየሠራሁ ራሴንም ሆነ ጓደኞቼን እረዳ እንደ ነበር እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የተባረከ ነው’ የሚለውን የጌታ ኢየሱስን ቃል በማስታወስ፥ በእጃችን እየሠራን ደካሞችን መርዳት እንደሚገባን በብዙ መንገድ አሳይቻችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከሁሉም ጋር ተንበርክኮ ጸለየ። ሁሉም አለቀሱና ጳውሎስን ዐቅፈው ሳሙት። ይልቁንም በጣም ያዘኑት፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩም” ብሎአቸው ስለ ነበር ነው፤ እስከ መርከብ ድረስም ሸኙት።
የሐዋርያት ሥራ 20 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 20:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos