የሐዋርያት ሥራ 20:1-16

የሐዋርያት ሥራ 20:1-16 አማ05

ሁከቱ ጸጥ ካለ በኋላ ጳውሎስ ምእመናኑን በአንድነት አስጠርቶ በምክር ቃል አጽናናቸው፤ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ሄደ። በእነዚያ በሚያልፍባቸው ስፍራዎች ምእመናንን በብዙ ምክር እያበረታታ ወደ ግሪክ አገር ሄደ። እዚያም ሦስት ወር ቈየ፤ ከዚህ በኋላ በመርከብ ወደ ሶርያ ለመሄድ አሰበ፤ ግን አይሁድ በእርሱ ላይ ሤራ ማድረጋቸውን ባወቀ ጊዜ በመቄዶንያ በኩል ለመመለስ ወሰነ። የጲርሁስ ልጅ ሶጳጥሮስ ከቤርያ፥ አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ ከተሰሎንቄ፥ ጋይዮስ ከደርቤ፥ ጢሞቴዎስ፥ ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ ከእስያ አብረውት ሄዱ። እነርሱ ቀድመውን ሄደው በጢሮአዳ ቈዩን። እኛ ግን ከቂጣ በዓል በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተሳፍረን በአምስት ቀን እነርሱ ወዳሉበት ወደ ጢሮአዳ ደረስንና እዚያ ሰባት ቀን አሳለፍን። ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እንጀራ ቈርሶ በአንድነት ለመብላት ተሰበሰብን፤ ጳውሎስ በማግስቱ መሄድ ስለ ነበረበት ለተሰበሰቡት ሰዎች ይናገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት አስረዘመ። እኛ በተሰበሰብንበት ፎቅ ብዙ መብራት ነበር። ኤውጤኪስ የተባለ አንድ ወጣት በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን በማስረዘሙ ወጣቱ ከባድ እንቅልፍ ያዘው፤ እንቅልፍ ስላሸነፈውም ከሦስተኛው ፎቅ ወደ ታች ወደቀ፤ ሰዎች ባነሡት ጊዜ ሞቶ አገኙት። ነገር ግን ጳውሎስ ወርዶ በልጁ ላይ ጐንበስ በማለት አቀፈውና “ገና በሕይወት አለ፤ አትደንግጡ!” አለ። ጳውሎስ ወደ ፎቅ ተመልሶ ወጣና እንጀራ ቈርሶ ከአማኞች ጋር በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ከቈየ በኋላ ሄደ። ሰዎቹም የዳነውን ወጣት ወደ ቤት ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ። ጳውሎስን ለማሳፈር ስለ አሰብን እኛ ቀድመን በመርከብ ወደ አሶስ ሄድን፤ ይህንንም ያደረግነው ጳውሎስ እስከ አሶስ ድረስ በእግሩ ለመሄድ ስለ ወሰነና እንዲህ እንድናደርግ ስለ አዘዘን ነው። ከእርሱ ጋር በአሶስ በተገናኘን ጊዜ በመርከብ አሳፍረነው ወደ ሚጢሊኒ አብረን ሄድን። በማግስቱ ከዚያ ተነሥተን በኪዮስ ፊት ለፊት ወዳለው ስፍራ በመርከብ ደረስን፤ በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞስ ተሻገርንና በማግስቱ ወደ ሚሊጢ ደረስን። ጳውሎስ በእስያ ጊዜ እንዳያባክን ብሎ ኤፌሶንን አልፎ ለመሄድ ፈለገ፤ ይህንንም ያደረገው ለጰንጠቆስጤ በዓል በኢየሩሳሌም ለመገኘት አስቦ ስለ ነበር ነው።