በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ምድር ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፥ ይህን የሆነውን ነገር ለማወቅ ንግግሬን አዳምጡ፤ ከጠዋቱ ገና ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ እናንተ እንዳሰባችሁት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም። ነገር ግን ይህ የሆነው ነቢዩ ኢዩኤል እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ‘እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል፤ መንፈሴን በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። እንዲሁም በእነዚያ ቀኖች በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ። በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮችን፥ በታች በምድር ተአምራትን አሳያለሁ፤ ደም፥ እሳት፥ የጢስ ጭጋግም ይታያል። ታላቁና አስገራሚው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፥ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ደም ትመስላለች። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል አዳምጡ፤ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት የናዝሬቱ የኢየሱስ ማንነት እግዚአብሔር በእናንተ መካከል በእርሱ አማካይነት በፈጸማቸው ታላላቅ ሥራዎች፥ ተአምራትና ምልክቶች ተረጋግጦአል። እርሱም ራሱ እግዚአብሔር አስቀድሞ ባቀደውና ባወቀው አሠራር መሠረት ለእናንተ ተላልፎ ተሰጠ፤ እናንተም በዐመፀኞች እጅ እንዲሰቀልና እንዲሞት አደረጋችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ኀይል አስወግዶ ከሞት አስነሣው፤ ስለዚህም ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለም። ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልናወጥም እርሱ በቀኜ ነው ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም በደስታ ተሞላ፤ እንዲሁም ሟች የሆነው ሥጋዬ በተስፋ ይኖራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ ቅዱስህንም በመቃብር በስብሶ እንዲቀር አታደርገውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከእኔም ጋር በመሆንህ ደስታዬ ፍጹም ይሆናል።’ “ወንድሞቼ ሆይ! ከቀድሞ አባቶች አንዱ የሆነው ዳዊት እንደ ሞተና እንደ ተቀበረ፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ እንዳለ በግልጥ ልንገራችሁ። ነገር ግን ዳዊት ይህን የተናገረው ነቢይ ስለ ነበረና እግዚአብሔር ‘ከዘርህ አንዱን በዙፋንህ ላይ አስቀምጥልሃለሁ’ ሲል በመሐላ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያውቅ ስለ ነበር ነው፤ በዚህም ምክንያት መሲሕ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም በመቃብር በስብሶ እንደማይቀር አስቀድሞ አይቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። በእግዚአብሔር ቀኝ ለመቀመጥ ከፍ ባለ ጊዜና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ በተቀበለ ጊዜ ይህን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። እንግዲህ ወደ ሰማይ የወጣው ዳዊት ባለመሆኑ ዳዊት ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፤ ‘ጌታ ለጌታዬ (ለመሲሑ) ጠላቶችህን በሥልጣንህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ ብሎታል። “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታና መሲሕ እንዳደረገው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በእርግጥ ይወቅ!” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው በሐዘን ተነክቶ ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት፥ “ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአታችሁም ይቅር እንዲባልላችሁ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስንም ትቀበላላችሁ፤ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ ጌታ አምላካችን ወደ እርሱ ለሚጠራቸው፥ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነው።” በሌላም በብዙ ቃል እየመሰከረ፥ “በዚህ ጠማማ ትውልድ ላይ ከሚመጣው ቅጣት ራሳችሁን አድኑ!” በማለት መከራቸው።
የሐዋርያት ሥራ 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 2:14-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos