የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 19:21-41

የሐዋርያት ሥራ 19:21-41 አማ05

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ አስቦ “እዚያ ከደረስኩ በኋላ ወደ ሮም መሄድ አለብኝ” አለ። ስለዚህ ከሚያገለግሉት ሰዎች ሁለቱን፥ ጢሞቴዎስንና ኤራስጦስን ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ በእስያ ለጥቂት ቀኖች ቈየ። በዚያን ጊዜ በጌታ መንገድ ምክንያት በኤፌሶን ታላቅ ሁከት ተነሣ። አንድ ድሜጥሮስ የሚባል ብር አንጥረኛ የአርጤሚስን ቤተ መቅደስ ምስል ከብር እየሠራ ለአንጥረኞች ብዙ ትርፍ ያስገኝ ነበር። ስለዚህ ይህ ሰው አንጥረኞችንና የእነርሱ ዐይነት ሥራ ያላቸውን ሌሎችንም ሰዎች ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሰዎች! እኛ ሀብት የምናገኘው በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ፤ ይህ ጳውሎስ ‘በሰው እጅ የተሠሩ ምስሎች አማልክት አይደሉም’ እያለ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት አገሮች በቀር በመላዋ እስያ ምን ያኽል ብዙ ሕዝብ እንዳግባባና እንዳሳመነ እናንተ ራሳችሁ ያያችሁትና የሰማችሁት ነው። በዚህ ዐይነት ይህ የእኛ ሥራ መናቁ ነው፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በእስያና በመላው ዓለም ሰው ሁሉ የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤሚስ ቤተ መቅደስ ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ነው፤ የእርስዋም ታላቅነት መሻሩ ነው።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ተቈጥተው፥ “የኤፌሶን አርጤሚስ ታላቅ ናት!” እያሉ ጮኹ። ከተማዋም በሙሉ ተሸበረች፤ ሕዝቡም የመቄዶንያ ተወላጆች የሆኑትን ሁለቱን የጳውሎስን የጒዞ ጓደኞች፥ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው እየጐተቱ ወደ ሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ ሮጡ። ጳውሎስ ወደ ሕዝቡ ለመሄድ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን እንዳይሄድ ከለከሉት። ከእስያ አገር ባለሥልጣኖችም ወዳጆቹ የሆኑ አንዳንዶቹ ወደ ጳውሎስ ሰው ልከው “ወደ ሕዝብ መሰብሰቢያው ቦታ ሄደህ እንዳትታይ” ሲሉ ለመኑት። በሕዝቡ መካከል ታላቅ ሁከት ስለ ነበር አብዛኞቹ ለምን እንደ ተሰበሰቡ እንኳ አያውቁም ነበር፤ በዚህ ምክንያት አንዱ አንድ ነገር እያለ ሲጮኽ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር እያለ ይጮኽ ነበር። አንዳንድ የአይሁድ ወገኖች እስክንድር የተባለውን ሰው ከሕዝቡ ገፋፍተው ወደ ፊት አቀረቡት፤ ከሕዝቡም መካከል አንዳንዶቹ በደንብ እንዲከራከርላቸው መከሩት፤ እስክንድርም ሕዝቡ ጸጥ እንዲል በእጁ ጠቀሰና የመከላከያ ንግግር ለማድረግ ተዘጋጀ። ነገር ግን እስክንድር አይሁዳዊ መሆኑን ሰዎቹ ሁሉ ባወቁ ጊዜ “የኤፌሶን አርጤሚስ ታላቅ ናት!” እያሉ ሁለት ሰዓት ያኽል ሁሉም በአንድ ድምፅ ጮኹ። በመጨረሻ የከተማይቱ ዋና ጸሐፊ፥ ሕዝቡን ዝም አሰኘና እንዲህ አለ፦ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ! የኤፌሶን ከተማ ነዋሪዎች፥ የታላቂቱን አርጤሚስን ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደውን ምስልዋን እንደሚጠብቁ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ይህን የሚክድ ማንም ስለሌለ ጸጥ እንድትሉና በችኰላ ክፉ ነገር ከማድረግ እንድትጠነቀቁ ይገባል። ቤተ መቅደስን ያልዘረፉትንና በአምላካችን ላይ የስድብ ቃል ያልተናገሩትን ሰዎች ወደዚህ ይዛችሁ መጥታችኋል። ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች የሚከሱት ሰው ካለ ፍርድ የሚሰጥባቸው ቀኖች አሉ፤ ባለሥልጣኖችም አሉ፤ እዚያ ይሟገቱ። ሌላ የምትፈልጉት ነገር ካለ ግን በሕጋዊ ሸንጎ ይታያል። አለበለዚያ ዛሬ በተደረገው ነገር ‘ሁከት አስነሥተዋል’ ተብለን እንዳንከሰስ ያስፈራል፤ ‘ይህ ብጥብጥ በምን ምክንያት ተነሣ’ ተብለን ብንጠየቅ የምንሰጠው መልስ የለንም” ይህንንም ብሎ የተሰበሰቡት ሰዎች እንዲበተኑ አደረገ።