የሐዋርያት ሥራ 19:11-20

የሐዋርያት ሥራ 19:11-20 አማ05

እግዚአብሔር በጣም አስደናቂ የሆኑ ተአምራትን በጳውሎስ እጅ ያደርግ ነበር። በዚህም ምክንያት የጳውሎስን አካል የነካውን ልብስና መሐረብ እየወሰዱ በሽተኞቹን ሲያስነኩአቸው ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡላቸው ነበር። አጋንንትን ከሰዎች እያስወጡ በየቦታው የሚዞሩ አንዳንድ አይሁድ “ጳውሎስ በሚሰብከው በጌታ ኢየሱስ ስም እንድትወጡ እናዛችኋለን” በማለት አጋንንትን ከሰዎች ለማስወጣት ይሞክሩ ነበር። የአይሁድ ሊቀ ካህናት የሆነ የአስቄዋ ሰባት ልጆችም እንዲሁ ያደርጉ ነበር። ነገር ግን ርኩሱ መንፈስ “ኢየሱስን ዐውቃለሁ! ጳውሎስንም ዐውቃለሁ! ኧረ እናንተ እነማን ናችሁ?” አላቸው። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበትም ሰው ዘሎ በማነቅ በረታባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ቈስለውና ራቊታቸውን ሆነው ከቤት ሸሽተው ወጡ። ይህም ነገር በኤፌሶን በሚኖሩት አይሁድና አሕዛብ ዘንድ ስለ ተሰማ ሁሉም ፈሩ፤ የጌታ የኢየሱስም ስም እጅግ ገናና ሆነ። ከአማኞችም ብዙዎቹ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ እየተናዘዙ ይመጡ ነበር። ብዙ አስማተኞችም የአስማት መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው በሕዝቡ ሁሉ ፊት አቃጠሉአቸው፤ የመጽሐፎቹ ዋጋ ሲተመን ኀምሳ ሺህ ጥሬ ብር ሆኖ ተገኘ። በዚህ ዐይነት የጌታ ቃል በጣም እየተስፋፋና ድል እያደረገ ይሄድ ነበር።