የሐዋርያት ሥራ 19:1-41

የሐዋርያት ሥራ 19:1-41 አማ05

አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን ደረሰ፤ እዚያ ጥቂት ክርስቲያኖችን አገኘና “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችሁ ነበርን?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አልተቀበልንም፤ መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ ሰምተን አናውቅም” ሲሉ መለሱለት። ጳውሎስም “ታዲያ፥ ምን ዐይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?” አላቸው። እነርሱም “የዮሐንስን ጥምቀት ነው” አሉት። ጳውሎስም “የዮሐንስ ጥምቀትማ ንስሓ ስለ መግባት የተፈጸመ ነው፤ ለሕዝቡም የተናገረው ‘ከእኔ በኋላ በሚመጣው እመኑ’ እያለ ነበር፤ እርሱም ኢየሱስ ነው” አላቸው። ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። ጳውሎስ እጁን በጫነባቸውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረደና በሌላ ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትንም መናገር ጀመሩ። ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያኽል ነበሩ። ጳውሎስ ወደ ምኲራብ ሄዶ ለሦስት ወር ያኽል ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተከራከረና ሕዝቡን እያስረዳ በድፍረት ያስተምር ነበር። አንዳንዶች ግን እልኸኞች በመሆን የጌታን መንገድ በሕዝቡ ፊት እየተሳደቡ አናምንም ባሉ ጊዜ ከእነርሱ ራቀ፤ አማኞችንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ አዳራሽ በየቀኑ ያስተምር ነበር። ጳውሎስ ይህን ያደረገው ለሁለት ዓመት ያኽል ነው፤ በዚያም ጊዜ በእስያ የሚኖሩ አይሁድና አሕዛብ ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ። እግዚአብሔር በጣም አስደናቂ የሆኑ ተአምራትን በጳውሎስ እጅ ያደርግ ነበር። በዚህም ምክንያት የጳውሎስን አካል የነካውን ልብስና መሐረብ እየወሰዱ በሽተኞቹን ሲያስነኩአቸው ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡላቸው ነበር። አጋንንትን ከሰዎች እያስወጡ በየቦታው የሚዞሩ አንዳንድ አይሁድ “ጳውሎስ በሚሰብከው በጌታ ኢየሱስ ስም እንድትወጡ እናዛችኋለን” በማለት አጋንንትን ከሰዎች ለማስወጣት ይሞክሩ ነበር። የአይሁድ ሊቀ ካህናት የሆነ የአስቄዋ ሰባት ልጆችም እንዲሁ ያደርጉ ነበር። ነገር ግን ርኩሱ መንፈስ “ኢየሱስን ዐውቃለሁ! ጳውሎስንም ዐውቃለሁ! ኧረ እናንተ እነማን ናችሁ?” አላቸው። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበትም ሰው ዘሎ በማነቅ በረታባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ቈስለውና ራቊታቸውን ሆነው ከቤት ሸሽተው ወጡ። ይህም ነገር በኤፌሶን በሚኖሩት አይሁድና አሕዛብ ዘንድ ስለ ተሰማ ሁሉም ፈሩ፤ የጌታ የኢየሱስም ስም እጅግ ገናና ሆነ። ከአማኞችም ብዙዎቹ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ እየተናዘዙ ይመጡ ነበር። ብዙ አስማተኞችም የአስማት መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው በሕዝቡ ሁሉ ፊት አቃጠሉአቸው፤ የመጽሐፎቹ ዋጋ ሲተመን ኀምሳ ሺህ ጥሬ ብር ሆኖ ተገኘ። በዚህ ዐይነት የጌታ ቃል በጣም እየተስፋፋና ድል እያደረገ ይሄድ ነበር። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ አስቦ “እዚያ ከደረስኩ በኋላ ወደ ሮም መሄድ አለብኝ” አለ። ስለዚህ ከሚያገለግሉት ሰዎች ሁለቱን፥ ጢሞቴዎስንና ኤራስጦስን ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ በእስያ ለጥቂት ቀኖች ቈየ። በዚያን ጊዜ በጌታ መንገድ ምክንያት በኤፌሶን ታላቅ ሁከት ተነሣ። አንድ ድሜጥሮስ የሚባል ብር አንጥረኛ የአርጤሚስን ቤተ መቅደስ ምስል ከብር እየሠራ ለአንጥረኞች ብዙ ትርፍ ያስገኝ ነበር። ስለዚህ ይህ ሰው አንጥረኞችንና የእነርሱ ዐይነት ሥራ ያላቸውን ሌሎችንም ሰዎች ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሰዎች! እኛ ሀብት የምናገኘው በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ፤ ይህ ጳውሎስ ‘በሰው እጅ የተሠሩ ምስሎች አማልክት አይደሉም’ እያለ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት አገሮች በቀር በመላዋ እስያ ምን ያኽል ብዙ ሕዝብ እንዳግባባና እንዳሳመነ እናንተ ራሳችሁ ያያችሁትና የሰማችሁት ነው። በዚህ ዐይነት ይህ የእኛ ሥራ መናቁ ነው፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በእስያና በመላው ዓለም ሰው ሁሉ የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤሚስ ቤተ መቅደስ ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ነው፤ የእርስዋም ታላቅነት መሻሩ ነው።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ተቈጥተው፥ “የኤፌሶን አርጤሚስ ታላቅ ናት!” እያሉ ጮኹ። ከተማዋም በሙሉ ተሸበረች፤ ሕዝቡም የመቄዶንያ ተወላጆች የሆኑትን ሁለቱን የጳውሎስን የጒዞ ጓደኞች፥ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው እየጐተቱ ወደ ሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ ሮጡ። ጳውሎስ ወደ ሕዝቡ ለመሄድ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን እንዳይሄድ ከለከሉት። ከእስያ አገር ባለሥልጣኖችም ወዳጆቹ የሆኑ አንዳንዶቹ ወደ ጳውሎስ ሰው ልከው “ወደ ሕዝብ መሰብሰቢያው ቦታ ሄደህ እንዳትታይ” ሲሉ ለመኑት። በሕዝቡ መካከል ታላቅ ሁከት ስለ ነበር አብዛኞቹ ለምን እንደ ተሰበሰቡ እንኳ አያውቁም ነበር፤ በዚህ ምክንያት አንዱ አንድ ነገር እያለ ሲጮኽ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር እያለ ይጮኽ ነበር። አንዳንድ የአይሁድ ወገኖች እስክንድር የተባለውን ሰው ከሕዝቡ ገፋፍተው ወደ ፊት አቀረቡት፤ ከሕዝቡም መካከል አንዳንዶቹ በደንብ እንዲከራከርላቸው መከሩት፤ እስክንድርም ሕዝቡ ጸጥ እንዲል በእጁ ጠቀሰና የመከላከያ ንግግር ለማድረግ ተዘጋጀ። ነገር ግን እስክንድር አይሁዳዊ መሆኑን ሰዎቹ ሁሉ ባወቁ ጊዜ “የኤፌሶን አርጤሚስ ታላቅ ናት!” እያሉ ሁለት ሰዓት ያኽል ሁሉም በአንድ ድምፅ ጮኹ። በመጨረሻ የከተማይቱ ዋና ጸሐፊ፥ ሕዝቡን ዝም አሰኘና እንዲህ አለ፦ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ! የኤፌሶን ከተማ ነዋሪዎች፥ የታላቂቱን አርጤሚስን ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደውን ምስልዋን እንደሚጠብቁ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ይህን የሚክድ ማንም ስለሌለ ጸጥ እንድትሉና በችኰላ ክፉ ነገር ከማድረግ እንድትጠነቀቁ ይገባል። ቤተ መቅደስን ያልዘረፉትንና በአምላካችን ላይ የስድብ ቃል ያልተናገሩትን ሰዎች ወደዚህ ይዛችሁ መጥታችኋል። ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች የሚከሱት ሰው ካለ ፍርድ የሚሰጥባቸው ቀኖች አሉ፤ ባለሥልጣኖችም አሉ፤ እዚያ ይሟገቱ። ሌላ የምትፈልጉት ነገር ካለ ግን በሕጋዊ ሸንጎ ይታያል። አለበለዚያ ዛሬ በተደረገው ነገር ‘ሁከት አስነሥተዋል’ ተብለን እንዳንከሰስ ያስፈራል፤ ‘ይህ ብጥብጥ በምን ምክንያት ተነሣ’ ተብለን ብንጠየቅ የምንሰጠው መልስ የለንም” ይህንንም ብሎ የተሰበሰቡት ሰዎች እንዲበተኑ አደረገ።