የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 17

17
በተሰሎንቄ የተነሣ ሁከት
1ጳውሎስና ሲላስ በአንፊጶሊስና በአጶሎንያ አልፈው ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ፤ እዚያም የአይሁድ ምኲራብ ነበረ። 2ጳውሎስ እንደ ልማዱ ወደ ምኲራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም አከታትሎ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ለሕዝብ ያስረዳ ነበር። 3መሲሕ መከራ መቀበልና ከሞት መነሣት እንደሚገባው ገልጦ እያስረዳ “ይህ እኔ የማበሥራችሁ ኢየሱስ መሲሕ ነው” ይል ነበር። 4ስለዚህ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ቃሉን ተረድተው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚያመልኩ እጅግ ብዙ አሕዛብ በከተማው የታወቁ ብዙ ሴቶች ቃሉን ተረድተው ተባበሩ።
5አይሁድ ግን ቀንተው የሚበጠብጡ ሥራ ፈቶችን ከየመንገዱ ሰበሰቡና አሳደሙ። በከተማው ውስጥ ብጥብጥ እንዲነሣ አደረጉ፤ ጳውሎስንና ሲላስን አውጥተው ለሕዝቡ ለመስጠትም የኢያሶንን ቤት ከበቡ። 6ነገር ግን እነርሱን ባጡአቸው ጊዜ ኢያሶንንና አንዳንድ አማኞችን ለከተማው ባለሥልጣኖች ለማቅረብ እየጐተቱ ወሰዱአቸው፤ እንዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ “እነዚህ ዓለምን ሁሉ ያወኩ ሰዎች አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል! 7ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ እያሉም የሮምን ንጉሠ ነገሥት ትእዛዝ ይቃወማሉ።” 8ሕዝቡና የከተማው ባለሥልጣኖች ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ። 9ኢያሶንንና ሌሎቹንም ዋስ አስጠርተው ለቀቁአቸው።
ጳውሎስና ሲላስ በቤርያ
10ወንድሞች በቶሎ ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ እንዲሄዱ አደረጉአቸው፤ እዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ። 11በቤርያ ያሉት አይሁድ በተሰሎንቄ ካሉት ይልቅ ቅን አመለካከት ያላቸው ስለ ነበሩ ቃሉን በታላቅ ደስታ ተቀበሉ፤ የቃሉንም እውነተኛነት ለማረጋገጥ በየቀኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር። 12ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎች አመኑ፤ ብዙዎች የግሪክ ሀብታሞች ሴቶችና ብዙዎች ግሪካውያን ወንዶችም አመኑ። 13ነገር ግን በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ጳውሎስ በቤርያም የእግዚአብሔርን ቃል እንዳበሠረ ባወቁ ጊዜ ወደዚያ መጡና ሕዝቡን አሳድመው ብጥብጥ አስነሡ። 14በዚህ ጊዜ ወንድሞች በቶሎ ጳውሎስ ወደ ባሕሩ አጠገብ እንዲሄድ አደረጉት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው በቤርያ ቀሩ። 15ጳውሎስን የሸኙት ሰዎች እስከ አቴና አደረሱት “ሲላስና ጢሞቴዎስ ሳይዘገዩ በቶሎ ወደ እኔ ይምጡልኝ” የሚለውንም የጳውሎስን ትእዛዝ ይዘው ወደ ቤርያ ተመለሱ።
ጳውሎስ በአቴና
16ጳውሎስ በአቴና ሆኖ ሲላስንና ጢሞቴዎስን ሲጠብቅ ሳለ በከተማዋ ጣዖት መሙላቱን በተመለከተ ጊዜ በመንፈሱ ተበሳጨ። 17ስለዚህ በምኲራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርንም ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር በአደባባይም በየቀኑ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይከራከር ነበር። 18ኤፒኮሮሶችና እስቶይኮች የተባሉ ፈላስፎችም ወደ እርሱ እየመጡ ይከራከሩ ነበር። አንዳንዶቹ “ይህ ለፍላፊ ምን ማለት ይፈልጋል?” ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ “ስለ አዳዲስ አማልክት የሚናገር ይመስላል” ይሉ ነበር፤ ይህንንም ያሉበት ምክንያት ጳውሎስ የኢየሱስንና የትንሣኤውን መልካም ዜና ስላበሠረ ነው። 19ስለዚህ ጳውሎስን ይዘው አርዮስፋጎስ በተባለው ስፍራ ወደሚሰበሰበው ጉባኤ አመጡትና እንዲህ አሉት፤ “ይህ አንተ የምታስተምረው አዲስ ትምህርት ምን እንደ ሆነ ማወቅ እንችላለንን? 20አንዳንድ እንግዳ ነገሮችን አሰምተኸናል፤ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ማወቅ እንፈልጋለን።” 21ይህን ያሉት የአቴና ነዋሪዎችና በአቴና የሚኖሩ የውጪ አገር ሰዎች ሁሉ አዲስ ነገር በመናገርና በመስማት ብቻ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይወዱ ስለ ነበር ነው።
22በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ጉባኤ ፊት ቆመና እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ! በሁሉም በኩል በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን ተረድቼአለሁ፤ 23በከተማችሁ እየተዘዋወርኩ የአምልኮ ስፍራዎቻችሁን ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ ተብሎ የተጻፈበትን የመሠዊያ ቦታ አገኘሁ፤ እንግዲህ እኔ አሁን የምነግራችሁ ስለዚሁ ሳታውቁ ስለምታመልኩት አምላክ ነው። 24እርሱ ዓለምንና በዓለም ያለውንም ሁሉ የፈጠረ ነው፤ የሰማይና የምድርም ጌታ ነው፤ እርሱ በሰው እጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ አይኖርም፤ 25ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌሎችንም ነገሮች ለሰው ሁሉ የሚሰጥ እርሱ ስለ ሆነ ምንም ነገር አይጐድለውም፤ የሰውም ርዳታ አያስፈልገውም። #1ነገ. 8፥27፤ ኢሳ. 42፥5። 26እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤ የተወሰኑ ዘመኖችንና የሚኖሩባቸውንም ቦታዎች መደበላቸው። 27ይህንንም ያደረገው ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉና በመመራመርም ፈልገው እርሱን ማግኘት እንዲችሉ ነው፤ ሆኖም እርሱ ከእኛ ከእያንዳንዳችን ሩቅ ነው ማለት አይደለም።
28‘ሕይወት የምናገኘውና የምንንቀሳቀሰው፥
የምንኖረውም በእርሱ ነው፤’
ይህም የእናንተ ባለ ቅኔዎች
‘እኛ ሁላችን የእርሱ ልጆች ነን’ እንዳሉት ነው።
29እንግዲህ እኛ የእርሱ ልጆች ከሆንን ‘እግዚአብሔር በሰው ጥበብና አሳብ ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከድንጋይ የተሠራውን ቅርጽ ይመስላል’ ብለን ማሰብ አይገባንም። 30እንግዲህ ሰዎች በቀድሞ ዘመን ባለማወቅ ያደረጉትን እግዚአብሔር ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየአገሩ ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አዞአል፤ 31እርሱ በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ሁሉ ላይ በእውነት የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአል፤ ይህንንም ለሁሉም ያረጋገጠው ያን የመረጠውን ሰው ከሞት በማስነሣቱ ነው።”
32“ከሞት መነሣት” የሚለውን ቃል በሰሙ ጊዜ አንዳንዶች አፌዙበት፤ ሌሎች ግን “ስለዚህ ጉዳይ ስትናገር ሌላ ጊዜ እንሰማለን” አሉት። 33ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከጉባኤው ወጥቶ ሄደ፤ 34አንዳንድ ሰዎች ግን ከእርሱ ጋር ተባበሩና አመኑ፤ ካመኑትም ሰዎች መካከል የአርዮስፋጎስ ጉባኤ አባል የሆኑት ዲዮናስዮስ የተባለ ሰውና ደማሪስ የተባለች አንዲት ሴት፥ ሌሎችም ይገኙባቸዋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ