ጳውሎስ ወደ ደርቤና ወደ ልስጥራ ሄደ፤ በልስጥራ ጢሞቴዎስ የሚባል አማኝ ይኖር ነበር፤ እናቱ አይሁዳዊት ክርስቲያን ነበረች፤ አባቱ ግን አረማዊ ነበር። ጢሞቴዎስ በልስጥራና በኢቆንዮን ባሉት ወንድሞች ዘንድ መልካም ዝና ነበረው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ይዞ መሄድ ስለ ፈለገ በዚያ ስፍራ በነበሩት አይሁድ ምክንያት እንዲገረዝ አደረገው፤ ይህንንም ያደረገው እነርሱ የጢሞቴዎስ አባት አረማዊ መሆኑን ያውቁ ስለ ነበረ ስለ እነርሱ ብሎ ነው። ጳውሎስና ሲላስ በየከተማው ሲያልፉ በኢየሩሳሌም ባሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የተወሰነውን ደንብ ለአማኞች ያስታውቁ ነበር፤ በሥራ ላይ እንዲያውሉትም ያሳስቡአቸው ነበር። ስለዚህ አብያተ ክርስቲያን በእምነት ጠነከሩ፤ ቊጥራቸውም በየቀኑ እየጨመረ ይሄድ ነበር። ጳውሎስና ሲላስ በእስያ ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አድርገው አለፉ፤ ወደ ሚስያ ድንበር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታኒያ ለመሄድ አስበው ነበር፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ ወደዚያ እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም። ስለዚህ በሚስያ በኩል አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። እዚያ በሌሊት አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን!” እያለ ሲለምነው ጳውሎስ በራእይ አየ። ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ ወዲያውኑ ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን፤ ይህም የሆነው ለመቄዶንያ ሰዎችም ወንጌልን እንድናስተምር ጌታ እንደ ጠራን ስለ ተረዳን ነው። ከጢሮአዳ በመርከብ ተሳፍረን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ ሄድን፤ በማግስቱም ወደ ናጱሌ ሄድን። ከዚያም ተነሥተን ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ ፊልጵስዩስ በመቄዶንያ የምትገኝ ታላቅ ከተማና የሮማውያን ቅኝ አገር ነበረች፤ በዚህችም ከተማ ጥቂት ቀኖች አሳለፍን። በሰንበትም ቀን ለጸሎት ይሰበሰቡበት ወደነበረው ከከተማው ውጪ ወደሚገኘው ወደ ወንዝ ዳር ሄድን፤ እዚያም ተቀምጠን ለተሰበሰቡት ሴቶች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማርን። ይሰሙን ከነበሩትም ሴቶች አንድዋ የትያጥሮን ከተማ ተወላጅ የሆነች የቀይ ልብስ ነጋዴ፥ ልድያ የምትባል ሴት ነበረች፤ እርስዋ እግዚአብሔርን የምታመልክ ሴት ነበረች፤ ጌታም ልቡናዋን ስለ ከፈተላት ጳውሎስ የሚናገረውን ቃል ታዳምጥ ነበር፤ እርስዋና በቤትዋ ያሉ ሰዎች ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ፥ “በጌታ የማምን መሆኔን ካረጋገጣችሁልኝ ወደ ቤቴ መጥታችሁ ተቀመጡ” ስትል አጥብቃ ለመነችን። አንድ ቀን ወደ ጸሎት ቦታ ስንሄድ ወደፊት የሚሆነውን ነገር በጥንቈላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ ያደረባት አንዲት አገልጋይ ልጃገረድ በመንገድ አገኘችን፤ ይህች ልጃገረድ በጥንቈላዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ትርፍ ታስገኝላቸው ነበር። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው! እነርሱ የመዳንን መንገድ ያበሥሩአችኋል!” በማለት ትጮኽ ነበር። ይህንንም ብዙ ቀን እየደጋገመች ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስ ግን ተበሳጨና ዞር ብሎ ርኩሱን መንፈስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርስዋ እንድትወጣ አዝሃለሁ!” አለው። ርኩሱም መንፈስ ወዲያውኑ ወጣ። አሳዳሪዎችዋ ጥቅም የሚያገኙበት ተስፋ እንደ ተቋረጠባቸው ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ያዙአቸው፤ እየጐተቱም ወደ አደባባይ ወሰዱአቸውና በሹሞች ፊት አቀረቡአቸው። ወደ ሮማውያን ባለሥልጣኖችም አመጡአቸውና እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ወገኖች ናቸው፤ በከተማችንም ሁከት ያስነሣሉ፤ እኛ የሮም ዜጋዎች ልንቀበለው ወይም ልናደርገው ያልተፈቀደልንን ሥርዓት ያስተምራሉ።” ሕዝቡም ሁሉ ተባብሮ በእነርሱ ላይ ተነሣ። ባለሥልጣኖችም የጳውሎስንና የሲላስን ልብስ ገፈፉና በዱላ እንዲደበደቡ አዘዙ። ብዙ ከተደበደቡም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አገቡአቸው፤ የወህኒ ቤቱም ጠባቂ በጥብቅ እንዲጠብቃቸው ታዘዘ። ጠባቂው ይህን ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፥ በወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገባቸው፤ እግሮቻቸውንም በግንድና ግንድ መካከል አጣብቆ አሰራቸው። ወደ እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ በጸሎትና በመዝሙር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎችም እስረኞች ያዳምጡአቸው ነበር። በድንገት የወህኒ ቤቱ መሠረት እስኪናጋ ድረስ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ በሮቹም ሁሉ በአንድ ጊዜ ተከፈቱ፤ የእያንዳንዱም እስረኛ ሰንሰለት ተፈታ። ጠባቂው ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ሊገድል ሰይፉን መዘዘ። ነገር ግን ጳውሎስ፥ “ሁላችንም እዚህ ነን! ስለዚህ በራስህ ላይ ጒዳት አታድርስ!” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጠባቂው መብራት አስመጥቶ እየሮጠ ወደ ውስጥ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ሥር በግንባሩ ተደፋ። ወደ ውጪም አወጣቸውና “ጌቶቼ ሆይ! ለመዳን ምን ማድረግ ይገባኛል?” አላቸው። እነርሱም “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ ትድናለህ፤ ቤተሰቦችህም ይድናሉ” አሉት። የጌታንም ቃል ለእርሱና በእርሱ ቤት ላሉትም ሁሉ ተናገሩ። በዚያኑ ሰዓት በሌሊት የወህኒ ቤቱ ጠባቂ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው፤ ወዲያውኑ እርሱና ቤተሰቡ በሙሉ ተጠመቁ። ከዚህ በኋላ ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤቱ ወስዶ ምግብ አቀረበላቸው፤ በእግዚአብሔር ስላመነም ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር ደስ አለው። በነጋም ጊዜ ባለሥልጣኖቹ “እነዚያ ሰዎች ይለቀቁ” ብለው ፖሊሶችን ላኩ። የወህኒ ቤት ጠባቂውም “እናንተ እንድትለቀቁ ባለሥልጣኖቹ ሰው ልከዋልና እንግዲህ ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ” ሲል ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስ ግን “እኛ የሮም ዜጋዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በአደባባይ ገርፈው ወደ ወህኒ አስገብተውናል። አሁን ደግሞ ከወህኒ ቤት በስውር እንድንወጣ ያደርጋሉን? አይሆንም! እነርሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን!” ሲል መለሰ። ፖሊሶቹ ይህን ነገር ለባለሥልጣኖቹ ነገሩ፤ ባለሥልጣኖቹም ጳውሎስና ሲላስ የሮም ዜጋዎች መሆናቸውን ባወቁ ጊዜ ፈሩ። ስለዚህ መጥተው ይቅርታ ጠየቁአቸውና ከወህኒ ቤት አስወጡአቸው፤ ከከተማውም እንዲሄዱ ለመኑአቸው። ጳውሎስና ሲላስም ከወህኒ ቤት ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፤ እዚያም ወንድሞችን አግኝተው፥ አጽናኑአቸውና ከተማውን ለቀው ሄዱ።
የሐዋርያት ሥራ 16 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 16:1-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos