በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ተብለው የሚጠሩ ሰባኪዎችና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፥ ጥቊር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉክዮስ፥ የአራተኛው ክፍል ገዢ የሄሮድስ አብሮ ዐደግ የነበረው ምናሔና ሳውል ነበሩ። እነርሱ ጌታን ሲያገለግሉና ሲጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “እኔ ለመረጥኳቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ!” አለ። እነርሱም ጾመውና ጸልየው እጆቻቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው። በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ሄዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። ወደ ሰላሚስ ከተማ በደረሱ ጊዜ በአይሁድ ምኲራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስ ማርቆስም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይረዳቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት አቋርጠው ወደ ጳፉ በደረሱ ጊዜ ባርየሱስ የሚባለውን አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ አገኙ፤ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር። የሚኖረውም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አስተዋይ አገረ ገዢ ጋር ነበረ፤ ይህ አገረ ገዢ በርናባስንና ሳውልን አስጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈለገ። ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ “ኤሊማስ” ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ ባርየሱስ አገረ ገዢው እንዳያምን ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፦ “አንተ የዲያብሎስ ልጅ! የእውነት ሁሉ ጠላት! ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፥ ቀጥተኛውን የጌታን መንገድ ማጣመም አትተውምን! አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። አገረ ገዢውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ አመነ፤ ስለ ጌታ በሰማውም ትምህርት ተደነቀ።
የሐዋርያት ሥራ 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 13:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች