የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

3 የዮሐንስ መልእክት 1

1
1በእውነት ለማፈቅረው፥ ለተወደደው ጋይዮስ፥
ከእኔ ከሽማግሌው የተላከ መልእክት፦ #ሐ.ሥ. 19፥29፤ ሮም 16፥23፤ 1ቆሮ. 1፥14።
2ወዳጄ ሆይ! ኑሮህ ሁሉ እንዲሳካልህ፥ ጤንነት እንዲኖርህና እንዲሁም የመንፈስ እርካታ እንድታገኝ እመኝልሃለሁ። 3ለእውነት ታማኝነትህንና በእውነትም መኖርህን አንዳንድ ክርስቲያን ወንድሞች መጥተው በነገሩኝ ጊዜ በጣም ደስ ተሰኘሁ። 4ልጆቼ በእውነት እየተመላለሱ መኖራቸውን ከመስማት የበለጠ የሚያስደስተኝ ነገር የለም።
የጋይዮስ መመስገን
5ወዳጄ ሆይ! ለአንተ እንግዶች ቢሆኑም እንኳ ለወንድሞች ታማኝ አገልግሎት ትሰጣለህ። 6እነርሱም ስለ አደረግህላቸው የፍቅር ሥራ በማኅበረ ምእመናን ፊት መስክረዋል፤ አሁንም እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ በጒዞአቸው ብትረዳቸው መልካም ነው። 7እነርሱ ክርስቶስን ለማገልገል ሲወጡ ከአሕዛብ ምንም ርዳታ አልተቀበሉም። 8የእውነት ሥራ ተካፋዮች እንድንሆን እንደእነዚህ ያሉትን ሰዎች መርዳት አለብን።
የዲዮትሬፊስ መወቀስና የድሜጥሮስ መመስገን
9ከዚህ በፊት ለቤተ ክርስቲያን ደብዳቤ ጽፌአለሁ፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን መሪ መሆን የሚፈልገው ዲዮትሬፊስ አሳቤን አልተቀበለም። 10ስለዚህ ወደ እናንተ ስመጣ እርሱ እየሰደበንና እያዋረደን ያደረገውን ክፉ ሥራ ሁሉ ለሁሉም እናገራለሁ፤ ይህም ሳይበቃው ቀርቶ፤ እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም። ሌሎችም እንዳይቀበሉአቸው ይከለክላል። ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል።
11ወዳጄ ሆይ! ደጉን ምሰል እንጂ ክፉውን አትምሰል። ደግ ሥራ የሚሠራ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። ክፉ ሥራ የሚሠራ ግን እግዚአብሔርን አላየውም።
12ለድሜጥሮስ ሰው ሁሉ በመልካም ይመሰክርለታል። እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች። እኛም እንመሰክርለታለን፤ የእኛም ምስክርነት እውነት መሆኑን ታውቃለህ።
የመጨረሻ ሰላምታ
13ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን በደብዳቤ ልገልጽልህ አልፈልግም። 14በቅርቡ ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ ቃል በቃል እንነጋገራለን።
15ሰላም ለአንተ ይሁን።
ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። አንተም ለወዳጆቻችን አንድ በአንድ ሰላምታ አቅርብልን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ