2 ወደ ጢሞቴዎስ 3:1-17

2 ወደ ጢሞቴዎስ 3:1-17 አማ05

በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ዕወቅ፤ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፥ ለገንዘብ የሚስገበገቡ፥ ትምክሕተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ ውለታቢሶች፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ይቅርታ የማያደርጉ፥ የሰው ስም የሚያጠፉ፥ ራሳቸውን የማይቈጣጠሩ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን ነገር የሚጠሉ፥ ከዳተኞች፥ ጥንቃቄ የሌላቸው፥ በትዕቢት የተነፉ፥ እግዚአብሔርን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ። እግዚአብሔርን የሚያመልኩ መስለው ይታያሉ፤ የአምልኮትን ኀይል ግን ይክዳሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ። እነዚህ ሰዎች በየቤቱ ሾልከው እየገቡ ብዙ ኃጢአት የተከመረባቸውንና በልዩ ልዩ ፍትወት የሚመሩ መንፈሰ ደካማ የሆኑ ሴቶችን እንደሚያጠምዱት ሰዎች ናቸው። እንዲህ ዐይነቶቹ ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ መድረስ አይችሉም። ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት እነዚህ ሰዎች አእምሮአቸው የተበላሸና በእምነትም ነገር ውድቀት የደረሰባቸው ስለ ሆነ እውነትን ይቃወማሉ። የኢያኔስና የኢያንበሬስ ሞኝነት እንደ ተገለጠ የእነዚህም ሰዎች ሞኝነት በሰው ሁሉ ፊት ስለሚገለጥ አይሳካላቸውም። አንተ ግን ትምህርቴን፥ አኗኗሬን፥ ዓላማዬን፥ እምነቴን፥ ትዕግሥቴን፥ ፍቅሬን፥ በያዝኩት መጽናቴን ተከትለሃል፤ እንዲሁም ስደቴንና መከራዬን ታውቃለህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የደረሰብኝን ነገርና በትዕግሥት የተቀበልኩትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከሁሉም አዳነኝ። የኢየሱስ ክርስቶስ ወገኖች ሆነው መንፈሳዊ ሕይወትን መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይገጥማቸዋል። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አስመሳዮች ግን ሰዎችን እያሳሳቱና ራሳቸውም እየተሳሳቱ፥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ አንተ ግን የተማርከው ከማን እንደ ሆነ ስለምታውቅ በተማርከውና እውነቱን በተረዳኸው ጽና። እንዲሁም ከሕፃንነትህ ጀምረህ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ትምህርት የሚሰጡህን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃል። ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፥ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ፥ ስሕተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል። የሚጠቅመውም የእግዚአብሔር ሰው ፍጹም እንዲሆንና ማንኛውንም መልካም ሥራ ለመሥራት ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።