ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3
3
1በዚህ ዐይነት በሳኦል ቤተሰብና በዳዊት ቤተሰብ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ለረጅም ጊዜ ቈየ፤ ሆኖም ዳዊት እየበረታ ሲሄድ የሳኦል ቤተሰብ እየተዳከመ ሄደ።
የዳዊት ልጆች
2ዳዊት በኬብሮን ሳለ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እነርሱም በኲሩ የኢይዝራኤል ተወላጅ ከሆነችው ከአሒኖዓም የተወለደው አምኖን፥ 3ሁለተኛው የቀርሜሎስ ተወላጅ የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጌል የተወለደው ኪልአብ፥ ሦስተኛው ታልማይ ተብሎ የሚጠራው የገሹር ንጉሥ ልጅ ከሆነችው ከማዕካ የተወለደው አቤሴሎም፥ 4አራተኛው ከሐጊት የተወለደው አዶኒያ፥ አምስተኛው ከአቢጣል የተወለደው ሸፋጥያ፥ 5ስድስተኛው ከሚስቱ ከዔግላ የተወለደው ዩትረዓም፥ እነዚህ ሁሉ በኬብሮን የተወለዱ ናቸው።
አበኔር ከዳዊት ጋር መተባበሩ
6በሳኦል ቤተሰብና በዳዊት ቤተሰብ መካከል ጦርነቱ እየቀጠለ በሄደ መጠን አበኔር በሳኦል ቤተሰብ እየበረታ ሄደ።
7ሳኦል የአያ ልጅ የሆነች ሪጽፋ የምትባል ቁባት ነበረችው፤ ኢያቡስቴ አበኔርን “ለምን ከአባቴ ቁባት ጋር ተገናኘህ” አለው። 8የኢያቡስቴ ቃል አበኔርን በጣም አስቈጣው፤ እንዲህም አለ፦ “እኔ ወደ ይሁዳ ነገድ የዞርኩ የማልጠቅም ውሻ ነኝን? እኔ ለአባትህ ቤት፥ ለወንድሞቹና ለወዳጆቹ ታማኝነትን አሳይቼአለሁ፤ አንተንም ለዳዊት አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ ታዲያ፥ አንተ ስለዚህች ሴት ትወቅሰኛለህን? 9-10እግዚአብሔር መንግሥትን ከሳኦል ቤት ወሰደ የዳዊትን ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ከሰሜን ከዳን ጀምሮ እስከ ደቡብ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ለመዘርጋት በመሐላ ቃል በገባለት መሠረት ባላስፈጽም በእኔ ላይ እግዚአብሔር ይፍረድ!” #1ሳሙ. 15፥28። 11ኢያቡስቴም እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፥ ለአበኔር አንድ ቃል እንኳ ሊመልስለት አልቻለም።
12አበኔር በዚያን ጊዜ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት መልእክተኞች ልኮ “የዚህች ምድር ገዢ የሚሆን ማነው? እንግዲህ ከእኔ ጋር ስምምነት አድርግ፤ እኔም መላው እስራኤል በአንተ ቊጥጥር ሥር እንዲሆን ለማድረግ እረዳሃለሁ” አለው።
13ዳዊትም “መልካም ነው! ከአንተ ጋር ስምምነት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንተ በቅድሚያ የምትፈጽምልኝ ነገር አለ፤ ይኸውም ወደ እኔ በምትመጣበት ጊዜ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ይዘህ ካልመጣህ መገናኘት አንችልም” አለው። 14እንዲሁም ዳዊት ወደ ኢያቡስቴ መልእክተኞች ልኮ እንዲህ አለው፤ “ሚስቴን ሜልኮልን መልስልኝ፤ እኔ እርስዋን ለማግባት የአንድ መቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ ጥያለሁ” አለው። #1ሳሙ. 18፥27። 15ስለዚህም ኢያቡስቴ መልእክተኛ በመላክ ሜልኮል የላዊሽ ልጅ ከሆነው ከባልዋ ከፓልጢኤል ልጅ አስወሰዳት፤ 16ባልዋ ፓልጢኤልም እያለቀሰ እስከ ባሑሪም ከተማ ድረስ ተከተላት፤ ነገር ግን አበኔር “ወደ ቤትህ ተመለስ” ባለው ጊዜ ተመለሰ።
17አበኔር ወደ እስራኤል መሪዎች ሄዶ እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት የእናንተ ንጉሥ እንዲሆን ለብዙ ጊዜ ተመኝታችሁ ነበር፤ 18እነሆ፥ አሁን አድርጉ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ‘በአገልጋዬ በዳዊት አማካይነት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያንና ከሌሎቹም ጠላቶቻቸው እጅ በመታደግ አድናለሁ’ ሲል ተናግሮ እንደ ነበር አስታውሱ።” 19አበኔር ለብንያም ነገድ ሕዝብም ይህንኑ ተናገረ፤ ከዚያም በኋላ የብንያምና የእስራኤል ሕዝብ ለማድረግ የተስማሙበትን ጉዳይ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ።
20አበኔር ኻያ ሰዎችን አስከትሎ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን በመጣ ጊዜ ዳዊት ግብዣ አደረገላቸው፤ 21አበኔርም ዳዊትን “ከአንተ ጋር እንዲነጋገሩና እንዲዋዋሉ አንተም ልብህ በተመኘው ሁሉ ላይ እንድትነግሥ ለማድረግ ወደ እስራኤላውያን ልሂድ” አለው። በዚህም ዐይነት ዳዊት አበኔርን በሰላም አሰናበተው።
የአበኔር መገደል
22ጥቂት ዘግየት ብሎ ኢዮአብና ሌሎች የዳዊት ወታደሮች ብዙ ምርኮ ካገኙበት ዘመቻ ተመለሱ፤ ይሁን እንጂ አበኔር በዚያን ጊዜ ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ሄዶ ስለ ነበር በኬብሮን አልነበረም፤ 23ኢዮአብና ተከታዮቹ በደረሱም ጊዜ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ ዳዊት መጥቶ ንጉሡ አበኔርን በሰላም እንዳሰናበተው ለኢዮአብ ነገሩት። 24ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? አበኔር ወደ አንተ መጥቶ ሳለ እንዲሁ እንዲሄድ ያሰናበትከው ስለምንድን ነው? 25የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ እርሱ የመጣው አንተን አታሎ የምትወጣበትንና የምትገባበትን ለማየትና ምን እንደምታደርግ ለመሰለል ነው።”
26ኢዮአብ ከዳዊት ፊት ወጥቶ ከሄደ በኋላ አበኔርን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ከሲራ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ መልሰው አመጡለት፤ ዳዊት ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። 27አበኔር ወደ ኬብሮን በደረሰ ጊዜ ኢዮአብ በግል ሊያነጋግረው የፈለገ በመምሰል ወደ ቅጽሩ በር ገለል አድርጎ ወሰደው፤ እዚያም ሆዱን ወግቶ ገደለው፤ ኢዮአብ ይህን ያደረገበት ምክንያት አበኔር ቀደም ብሎ ወንድሙን ዐሣሄልን ስለ ገደለበት ለመበቀል ነው። 28ዳዊትም የአበኔርን መገደል በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔና በንጉሣዊ ግዛቴ ውስጥ ያለው ሕዝብ ስለ አበኔር መገደል ከደሙ ንጹሓን መሆናችንን እግዚአብሔር ያውቃል። 29ስለዚህም ቅጣቱ በኢዮአብና በቤተሰቡ ላይ ይውረድ! በዘመናት ሁሉ ከቤተሰቡ የአባለ ዘር ወይም የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው አይጥፋ! እንዲሁም አካለ ስንኩል የሆነ ሰው፥ በጦር ሜዳ የሚሞት ወይም የሚበላው አጥቶ የሚራብ ሰው አይታጣ!” 30በዚህ ዐይነት ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳይ ወንድማቸውን ዐሣሄልን በገባዖን በተደረገው ጦርነት ስለ ገደለ አበኔርን ገደሉት።
የአበኔር በድን መቀበር
31ከዚህ በኋላ ዳዊት በሐዘን ልብሳቸውን ቀደው፥ ማቅ ለብሰው ለአበኔር እንዲያለቅሱ ኢዮአብንና የእርሱ ተከታዮች የሆኑትን ሰዎች አዘዘ፤ በቀብር ሥነ ሥርዓቱም ላይ ንጉሥ ዳዊት ራሱ አስክሬኑን ተከትሎ ሄደ፤ 32አበኔር በኬብሮን ተቀበረ፤ በመቃብሩም ላይ ንጉሡ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን በማየት በመረረ ሁኔታ አለቀሱ፤ 33ዳዊትም ለአበኔር ሐዘኑን በቅኔ ሲገልጥ እንዲህ አለ፦
“አበኔር እንደ ሞኝ ሰው ይሙትን?
34እጆችህ አልታሰሩም፤
እግሮችህ አልታበቱም፤
ታዲያ፥ በዚህ ሁኔታ ሳለ
በወንጀለኞች እጅ እንደሚወድቅ ሰው እንዴት ተገደልክ!”
ሕዝቡም ሁሉ ስለ እርሱ እንደገና አለቀሱ።
35ሰዎችም ቀኑን ሙሉ ዳዊት እህል ይቀምስ ዘንድ ለማግባባት ሞከሩ፤ እርሱ ግን “የዛሬይቱ ጀንበር ሳትጠልቅ እህል ብቀምስ እግዚአብሔር ይቅጣኝ!” ሲል ማለ። 36ሕዝቡም ሁሉ ይህን ነገር ተመልክተው ደስ አላቸው፤ በእርግጥም ንጉሡ ያደረገው ነገር ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው። 37የዳዊት ሰዎችና መላው የእስራኤል ሕዝብ በአበኔር ሞት ንጉሥ ዳዊት ምንም ያልተባበረ መሆኑን ተገነዘቡ። 38ንጉሡም ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች እንዲህ አለ፤ “በዛሬው ቀን በእስራኤል ታላቅ መሪ እንደ ሞተ አታስተውሉምን? 39ምንም እንኳ እኔ እግዚአብሔር መርጦ የሾመኝ ንጉሥ ብሆን ዛሬ ደካማነት ተሰምቶኛል፤ እነዚህ የጸሩያ ልጆች በእኔ ላይ እጅግ የበረቱ ዐመፀኞች ሆነውብኛል፤ እነዚህን ነፍሰ ገዳዮች እግዚአብሔር ራሱ የሚገባቸውን ቅጣት ይስጣቸው!”
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997