የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18

18
የአቤሴሎም ድል ተመቶ መሞት
1ንጉሥ ዳዊት ተከታዮቹን ሁሉ በአንድነት ከሰበሰበ በኋላ በሺህና በመቶ መድቦ ለእያንዳንዱ ቡድን የጦር መኰንን ሾመ፤ 2ከዚህም በኋላ ሦስት ክፍል አድርጎ ላካቸው፤ ኢዮአብን የሢሶው፥ አቢሳይ የሢሶው፥ እንዲሁም የጋት ተወላጅ የሆነው ኢታይ የሢሶው አዛዦች ሆኑ፤ ንጉሡም ተከታዮቹን “እኔም ራሴ አብሬአችሁ እሄዳለሁ” አላቸው።
3እነርሱም “አንተ ከእኛ ጋር መሄድ የለብህም፤ ጥቂቶቻችን ወደ ኋላ ተመልሰን ብንሄድ ወይም ግማሾቻችን ብንገደል ጠላት ምንም አይገደውም፤ አንተ ግን ከእኛ ዐሥሩን ሺህ ትበልጣለህ፤ ስለዚህ አንተ እዚሁ በከተማይቱ ውስጥ ቈይተህ አስፈላጊውን ርዳታ ብትልክልን ይሻላል” አሉት።
4ንጉሡም “እናንተ መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” ሲል መለሰላቸው። ከዚህ በኋላም በቅጽር በሩ አጠገብ ቆሞ በሺህና በመቶ የተመደቡት ሠራዊት ተሰልፈው ሲወጡ ተመለከተ። 5ለኢዮአብ፥ ለአቢሳና ለኢታይም “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ በአቤሴሎም ላይ ለሞት የሚያደርስ ጒዳት እንዳታደርሱበት” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው፤ ዳዊት ይህን ትእዛዝ ለጦር አዛዦቹ በሰጠ ጊዜም ወታደሮቹ ሁሉ ይሰሙ ነበር።
6የዳዊት ሠራዊት ወደ ገጠር ወጥተው እስራኤላውያንን በኤፍሬም ደን ውስጥ ተዋጉአቸው፤ 7እስራኤላውያንም በዳዊት ተከታዮች ድል ተመቱ፤ በዚያን ቀን የሞቱባቸው ሰዎች ቊጥር ኻያ ሺህ ያኽል ስለ ነበር የሽንፈታቸው ሁኔታ እጅግ አሠቃቂ ነበር፤ 8ጦርነቱም በየገጠሩ ስለ ተስፋፋ በጦርነት ከሞቱት ሰዎች ይልቅ በደን ውስጥ ያለቁት ቊጥራቸው በዛ።
9በድንገት፥ አቤሴሎም ከዳዊት ተከታዮች ጥቂቱን አገኘ፤ አቤሴሎም በዚያን ጊዜ በበቅሎ ላይ ተቀምጦ ይጋልብ ስለ ነበር በቅሎዋ በአንድ ትልቅ የወርካ ዛፍ ሥር ስታልፍ ሳለ የዛፉ ቅርንጫፍ የአቤሴሎምን ራስ ጠጒር ያዘበት፤ በቅሎዋም በእግሮቹ መኻል ሾልካ ስትሄድ አቤሴሎም በዐየር ላይ ተንጠልጥሎ ቀረ። #18፥9 የራስ ጠጒር፦ በዕብራይስጡ ራስ ተብሎአል። 10ከዳዊት ወታደሮችም አንዱ ይህን አይቶ ለኢዮአብ “ጌታዬ፤ አቤሴሎምን በወርካ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት!” ብሎ ነገረው።
11ኢዮአብም “ታዲያ ካየኸው ለምን ወዲያውኑ አልገደልከውም? ይህን አድርገህ ቢሆን ኖሮ እኔ ራሴ ዐሥር ጥሬ ብርና አንድ ዙር ዝናር በሸለምኩህ ነበር” ሲል መለሰለት።
12ሰውየው ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንድ ሺህ ጥሬ ብር እንኳ ብትሰጠኝ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሣም፤ ንጉሡ ለአንተ፥ ለአቢሳና ለኢታይ ‘ለእኔ ስትሉ በወጣቱ አቤሴሎም ላይ ለሞት የሚያደርስ ጒዳት እንዳታደርሱበት’ ሲል የሰጣችሁን ትእዛዝ ሁላችንም ሰምተናል፤ 13ታዲያ እኔ የንጉሡን ትእዛዝ በመጣስ አቤሴሎምን ገድዬ ቢሆን ኖሮ፥ ንጉሡ ሁሉን ነገር እንደሚሰማ ይህንንም መስማቱ አይቀርም፤ አንተም እኔን ለማዳን አትከላከልልኝም።”
14ኢዮአብም “እኔ አሁን ከአንተ ጋር ጊዜ ማባከን አልፈልግም” አለውና ሦስት ጦሮችን ወስዶ አቤሴሎም በወርካው ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት ሳለ በደረቱ ተከለበት። 15ከዚያም በኋላ የኢዮአብ አጃቢዎች ከሆኑ ወታደሮች ዐሥሩ ወደ አቤሴሎም ሄደው ዙሪያውን በመክበብ በጦር መሣሪያ ገደሉት።
16ኢዮአብ ጦርነቱ ይቆም ዘንድ እምቢልታ እንዲነፉ አዘዘ፤ ወታደሮቹም እስራኤላውያንን ከማሳደድ ተመልሰው መጡ፤ 17የአቤሴሎምንም ሬሳ ወስደው በደን ውስጥ በሚገኘው ጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በእርሱም ላይ ብዙ ትልልቅ ድንጋይ ከምረው እንዲሸፈን አደረጉት፤ እስራኤላውያንም ሁሉ ሸሽተው እያንዳንዱ ሰው ወደየቤቱ ገባ።
18አቤሴሎም ስሙን የሚያስጠራለት ወንድ ልጅ አልነበረውም፤ ስለዚህም በሕይወት በነበረበት ዘመን “የንጉሥ ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ለራሱ ሐውልት አሠርቶ ነበር፤ በራሱም ስም ሰይሞት ስለ ነበር እስከ ዛሬ ድረስ “የአቤሴሎም ሐውልት” እየተባለ ይጠራል።
ዳዊት የአቤሴሎምን ሞት መስማቱ
19ከዚህ በኋላ የሳዶቅ ልጅ አሒማዓጽ ኢዮአብን “እግዚአብሔር ከጠላቶቹ እንዳዳነው የሚገልጠውን መልካም ወሬ ይዤ ወደ ንጉሡ ልሩጥ” አለው።
20ኢዮአብም “አይሆንም፤ ዛሬ አንተ ይዘኸው የምትሄድ ምንም ዐይነት መልካም ወሬ የለም፤ ምናልባት ሌላ ቀን ይህን ልታደርግ ትችላለህ፤ ዛሬ ግን የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ ይህን ባታደርግ ይሻላል” አለው። 21ከዚህም በኋላ ኢዮአብ አገልጋዩ የነበረውን አንድ ኢትዮጵያዊ ጠርቶ “ያየኸውን ሁሉ ሄደህ ለንጉሡ ንገር” አለው፤ አገልጋዩም እጅ ነሥቶ ሮጠ።
22አሒማዓጽም “የፈለገው ነገር ቢሆን ግድ የለኝም፤ ስለዚህ እኔም ወሬውን እንዳደርስ ፍቀድልኝ” አለ።
ኢዮአብ ግን “ልጄ ሆይ፥ ስለምን ይህን ማድረግ ፈለግኽ? ይህን ስላደረግህ ምንም ሽልማት አታገኝም እኮ” አለው።
23አሒማዓጽም እንደገና “የፈለገው ነገር ቢሆን ግድ የለኝም፤ እኔ መሄድ እፈልጋለሁ” አለ።
ኢዮአብም “እንግዲያውስ ሂድ” አለው፤ ስለዚህም አሒማዓጽ በዮርዳኖስ ሸለቆ በሚያመራው መንገድ ሲሮጥ ሄዶ ወዲያውኑ ኢትዮጵያዊውን ቀደመው።
24ዳዊት በከተማይቱ ውስጣዊና ውጫዊ በሮች መካከል ባለው ግልጥ ቦታ ተቀምጦ ነበር፤ ጠባቂው በቅጥሩ በኩል ወደ ማማው ወጥቶ ስለ ነበር ቀና ብሎ ሲመለከት አንድ ሰው ብቻውን እየሮጠ ሲመጣ አየ፤ 25ዘበኛውም ድምፁንም በማሰማት ያየውን ለንጉሡ ነገረው፤ ንጉሡም “ብቻውን ከሆነ መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ፤ ያም ሯጭ ሰው እየቀረበ መጣ።
26ዘበኛውም እንደገና አንድ ሌላ ሰው እየሮጠ ሲመጣ አይቶ፥ የቅጽር በር ጠባቂውን በመጣራት “ተመልከት! ሌላም አንድ ሰው እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለው።
ንጉሡም “ይህኛውም መልካም ወሬ ይዞ የሚመጣ ሊሆን ይችላል” ሲል መለሰ።
27ዘበኛውም “የመጀመሪያው ሰው የሚሮጠው ልክ እንደ ሳዶቅ ልጅ አሒማዓጽ ነው” አለ። ንጉሡም “እርሱ ጥሩ ሰው ነው፤ መልካም ወሬ ይዞ ይመጣል” አለ።
28አሒማዓጽም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለንጉሡ ሰላምታ ሰጠ፤ በንጉሡም ፊት በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ “ንጉሥ ሆይ! በአንተ ላይ በዐመፅ የተነሣሡትን ድል እንድታደርግ ስለ ረዳህ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!” አለ።
29ንጉሡም “ወጣቱ አቤሴሎም ምንም ጒዳት አልደረሰበትምን?” ሲል ጠየቀ።
አሒማዓጽም “ጌታዬ ሆይ፥ የጦር አዛዥህ ኢዮአብ ወደ አንተ በላከኝ ጊዜ ታላቅ ሁካታ ሆኖ አየሁ፤ ነገር ግን ምን እንደ ሆነ መናገር አልችልም” ሲል መለሰ።
30ንጉሡም “እልፍ ብለህ ቁም” አለው። እርሱም እልፍ ብሎ ቆመ።
31ቀጥሎም ኢትዮጵያዊው አገልጋይ እዚያ ደረሰና ንጉሡን “ንጉሥ ሆይ! የምሥራች ቃል ይዤልህ መጥቼአለሁ፤ በአንተ ላይ በዐመፅ የተነሣሡብህን ድል እንድታደርግ ዛሬ እግዚአብሔር ረድቶሃል!” አለው።
32ንጉሡም “ወጣቱ አቤሴሎም ምንም ጒዳት አልደረሰበትምን?” ሲል ጠየቀ።
አገልጋዩም “ጌታዬ ሆይ! በእርሱ ላይ የደረሰ ነገር በጠላቶችህና በአንተ ላይ በዐመፁት ሁሉ ላይ ይድረስ!” ሲል መለሰ።
33ንጉሡም እጅግ አዘነ፤ በቅጽር በሩ አናት ላይ ወደሚገኘውም ክፍል ወጥቶ አለቀሰ፤ ወደዚያም ሲመጣ “ልጄ ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! አቤሴሎም ልጄ! ምነው በአንተ ምትክ እኔ በሞትኩ ልጄ ሆይ! አቤሴሎም ልጄ!” እያለ በመጮኽ ያለቅስ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ