እግዚአብሔር ነቢዩን ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ ናታንም ወደ ዳዊት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱ አንዱ ሀብታም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድኻ ነበር፤ ሀብታሙ ሰው ብዙ የቀንድ ከብቶችና የበግ መንጋ ነበሩት፤ ድኻው ግን በገንዘቡ የገዛት አንዲት የበግ ግልገል ብቻ ነበረችው፤ እርስዋን እየተንከባከበ ከልጆቹ ጋር በቤቱ ውስጥ ያሳድጋት ነበር፤ ከሚመገበው ይመግባት፥ ከሚጠጣውም ያጠጣት ነበር፤ ስትተኛም ያቅፋት ነበር፤ ያቺም ግልገል ልክ እንደ ልጁ ነበረች፤ አንድ ቀን ወደ ሀብታሙ ሰው ቤት አንድ መንገደኛ መጣ፤ ሀብታሙ ሰው ለእንግዳው የሚሆን ምግብ ለማዘጋጀት ከእንሰሶቹ አንዱን ማረድ አልፈለገም፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ የድኻውን ሰው ግልገል ወስዶ በማረድ ለእንግዳው ምግብ አዘጋጀ።” ዳዊት በሀብታሙ ሰው ታሪክ እጅግ ተቈጥቶ “ይህን ያደረገው ሰው ሞት እንደሚገባው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ይህን የመሰለ የጭካኔ ሥራ በመፈጸሙ ከዚያ ሰው የወሰደበትን አራት እጥፍ አድርጎ መመለስ አለበት” አለ። ናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ራስህ ነህ! የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ ንጉሥ አደረግኹህ፤ ከሳኦልም እጅ በመታደግ አዳንኩህ፤ መንግሥቱንና ሚስቶቹን ሰጠሁህ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ አነገሥኩህ፤ ይህም ሁሉ እንኳ የማይበቃህ ቢሆን ኖሮ በተጨማሪ እጥፍ አድርጌ በሰጠሁህ ነበር፤ ታዲያ ትእዛዜን የናቅኸው ስለምንድን ነው? ይህንንስ ክፉ ነገር ለምን አደረግህ? ኦርዮን በጦር ሜዳ አስገደልከው፤ ንጹሑን ሰው ዐሞናውያን እንዲገድሉት አደረግህ፤ ሚስቱንም ወሰድክ! አንተ ለእኔ ስላልታዘዝክ የኦርዮን ሚስት ስለ ወሰድክ፥ እነሆ ከቤትህ በሰይፍ የሚገደል አይጠፋም፤ ከቤተሰብህ አንዱ ተነሥቶ ችግር እንዲያደርስብህ የማደርግ መሆኔን በመሐላ አረጋግጥልሃለሁ፤ ሚስቶችህን ወስጄ ለሌላ ሰው በምሰጥበት ጊዜ ይህ ነገር እንደሚፈጸም ትገነዘባለህ፤ እርሱም ከሚስቶችህ ጋር በቀን ብርሃን ይገናኛል። አንተ ይህን ኃጢአት በስውር ሠርተሃል፤ እኔ ግን እስራኤል ሁሉ ይመለከቱ ዘንድ ይህን ነገር የቀን ብርሃን ባለበት በግልጥ አደርጋለሁ።’ ” ዳዊትም “ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዝኛለሁ” አለ። ናታንም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እግዚአብሔር ይቅር ስላለህ አትሞትም፤ ነገር ግን ይህን በደል በመፈጸም እግዚአብሔርን ስለ ናቅህ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ከዚህ በኋላ ናታን ወደ ቤቱ ሄደ። የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ እግዚአብሔር በከባድ ሕመም ቀሠፈው፤ ዳዊትም ሕፃኑን እንዲፈውስለት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ለመነ፤ በየሌሊቱም ወደ መኝታ ክፍሉ እየገባ በመሬት ላይ ይተኛ ነበር፤ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች ወደ እርሱ ቀርበው ከመሬት ላይ ሊያስነሡት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከመሬት ላለመነሣትና ከእነርሱም ጋር ምንም ነገር ላለመቅመስ ወሰነ፤ ከአንድ ሳምንትም በኋላ ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት ባለሟሎችም መርዶውን ለመንገር ፈርተው “ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ እንኳ ዳዊት ስንመክረው አልሰማንም፤ ታዲያ፥ አሁን የልጁን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? ምናልባት በራሱ ላይ አንዳች ጒዳት ማድረስ ይችል ይሆናል!” አሉ። ዳዊት እርስ በርሳቸው ሲያንሾካሹኩ በሰማ ጊዜ ሕፃኑ መሞቱን ተረዳ፤ ስለዚህም “ሕፃኑ ሞተ እንዴ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አዎ ሞቶአል” ሲሉ መለሱለት። ዳዊትም ከተኛበት መሬት ተነሥቶ ሰውነቱን ታጠበ፤ ቅባት ተቀባ፤ ልብሱንም ለወጠ፤ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄዶ ሰገደ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም ሲመለስ ምግብ እንዲያቀርቡለት ጠየቀ፤ እንደ ቀረበለትም ወዲያውኑ ተመገበ፤ ባለሟሎቹም “ይህ ነገር ምን እንደ ሆነ ለማወቅ አልቻልንም፤ ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ በመጾም አለቀስክለት፤ እርሱ ከሞተ በኋላ ግን ወዲያውኑ ተነሥተህ ተመገብክ!” አሉት። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕፃኑ በሕይወት ሳለ መጾሜና ማልቀሴ እርግጥ ነው፤ እግዚአብሔር ምሕረት አድርጎልኝ ሕፃኑ እንዳይሞት ያደርግ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፤ አሁን ግን ከሞተ በኋላ ስለምን እጾማለሁ? ሕፃኑን እንደገና በሕይወት እንዲኖር ማድረግ ይቻለኛልን? እኔ አንድ ቀን ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ ተመልሶ አይመጣም።” ከዚህ በኋላ ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ከእርስዋም ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ዳዊትም የልጁን ስም “ሰሎሞን” ብሎ ጠራው፤ እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደው፥ “ይዲድያ” የሚል ስም እንዲያወጣለት ነቢዩ ናታንን አዘዘው፤ ይህም “በእግዚአብሔር የተወደደ” ማለት ነው።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos