ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 21:1-26

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 21:1-26 አማ05

ምናሴ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኀምሳ አምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሔፍጺባ ተብላ የምትጠራ ነበረች፤ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ አገር በሚገቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋቸውን የአሕዛብን አሳፋሪ ልማድ በመከተል ምናሴ የሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ምናሴ አባቱ ሕዝቅያስ ደምስሶአቸው የነበሩትን የአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎች እንደገና እንዲሠሩ አደረገ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ባደረገውም ዐይነት ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሠዊያዎችን፥ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስልን ሠራ፤ የሰማይ ከዋክብትንም አመለከ። እግዚአብሔር እንዲመለክበት ባዘዘው ስፍራ ማለትም በቤተ መቅደስ ውስጥ አረማዊ መሠዊያዎችን አቆመ። በሁለቱም የቤተ መቅደሱ አደባባዮች የሰማይ ከዋክብት የሚመለኩባቸውን መሠዊያዎች ሠራ፤ የገዛ ልጁንም መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እርሱም ራሱ ሟርተኛና አስማተኛ ሆኖ ከጠንቋዮችና ከሙታን ጠሪዎች ምክርን ይጠይቅ ነበር፤ በዚህም ሁሉ አድራጎቱ ታላቅ ኃጢአት በመሥራቱ የእግዚአብሔርን ቊጣ አነሣሣ። በቤተ መቅደሱም ውስጥ የአሼራን ምስል አኖረ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን “ይህ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ እኔ ለዘለዓለም እመለክበት ዘንድ ከዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ የመረጥኩት ስፍራ ነው፤ የእስራኤል ሕዝብ ትእዛዞቼን ቢጠብቁና ለአገልጋዬ ለሙሴ የሰጠሁትንም ሕግ ቢፈጽሙ፥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ከዚህች ምድር ተነቃቅለው እንዲጠፉ አላደርግም” ሲል ነግሮአቸው የነበረው ነው፤ የይሁዳ ሰዎች ግን ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ይልቁንም ምናሴ እስራኤላውያን ወደፊት እየገፉ ሲመጡ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸው ሕዝቦች ይፈጽሙት ከነበረው ይበልጥ ወደ ከፋ ኃጢአት መራቸው። እግዚአብሔርም በአገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አሳፋሪ ነገር አደረገ፤ ይኸውም ቀድሞ ከነዓናውያን ይፈጽሙት ከነበረው ሁሉ የከፋ ነው፤ በሠራቸውም ጣዖቶች የይሁዳን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ፤ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እኔ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የማመጣው በጣም ከባድ መቅሠፍት ይህ ነው፤ ስለ እርሱም የሚሰማ ሰው ሁሉ በድንጋጤ ጭው ይላል፤ ሰማርያንና የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ከነዘሮቹ እንደ ቀጣሁ ሁሉ ኢየሩሳሌምንም እቀጣለሁ፤ ሳሕን ከተወለወለ በኋላ ተደፍቶ እንደሚቀመጥ፥ እኔም ኢየሩሳሌምን ከኃጢአት አጸዳታለሁ። ከጥፋት የተረፈውን ሕዝቤን ለጠላቶቹ ተላልፎ እንዲሰጥ እተወዋለሁ፤ እርሱም ይማረካል፤ ንብረቱም ይዘረፋል። በእነርሱም ላይ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ኃጢአት ሠርተው እኔን በማሳዘናቸውና ቊጣዬን በማነሣሣታቸው ነው።” ምናሴ የይሁዳን ሕዝብ ወደ ጣዖት አምልኮና እግዚአብሔርን ወደሚያሳዝን ኃጢአት ከመምራት አልፎ፥ ንጹሓን የሆኑትን ብዙ ሰዎችን በመፍጀት የኢየሩሳሌምን መንገዶች በደም እንዲጥለቀለቁ አድርጎአል። ምናሴ ያደረገው ሌላው ነገርና የፈጸመው ኃጢአት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ምናሴ ሞተ፤ በቤተ መንግሥቱ ግቢ “የዑዛ የአትክልት ስፍራ” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሞን ነገሠ። አሞን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ፥ ዕድሜው ኻያ ሁለት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም መሹሌሜት ተብላ የምትጠራ የያጥባ ከተማ ተወላጅ የሐሩጽ ልጅ ነበረች፤ አሞን እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ። የአባቱንም መጥፎ አርአያነት ሁሉ ተከተለ፤ አባቱ ይሰግድላቸው የነበሩትንም ጣዖቶች አመለከ፤ የቀድሞ አባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርንም ተወ፤ ለእግዚአብሔርም ቃል ለመታዘዝን ፈቃደኛ አልሆነም። ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም በአሞን ላይ አድመው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት፤ የይሁዳም ሕዝብ የአሞንን ገዳዮች ደምስሰው ልጁን ኢዮስያስን አነገሡ። አሞን ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። አሞን “የዑዛ የአትክልት ስፍራ” ተብሎ በሚጠራው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ።