ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 2:19-25

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 2:19-25 አማ05

ጥቂት ሰዎች ከኢያሪኮ ወደ ኤልሳዕ መጥተው “ጌታችን አንተ እንደምታውቀው ይህች ምድር መልካም ናት፤ ውሃው ግን መጥፎ በመሆኑ ምድሪቱ ምርት አትሰጥም” አሉት። ኤልሳዕም “በአዲስ አፍላል ማሰሮ ውስጥ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” ብሎ አዘዘ። እነርሱም እንዳዘዛቸው አድርገው አመጡለት። እርሱም ወደ ምንጩ ሄዶ ጨውን በውሃው ውስጥ በመጨመር፥ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ‘እኔ ይህን ውሃ በመፈወስ ንጹሕ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ የሞትና የምርት አልባነት ምክንያት አይሆንም’ ” ሲል ተናገረ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤልሳዕ በተናገረው መሠረት ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ ንጹሕ ነው። ኤልሳዕም ወደ ቤትኤል ለመሄድ ከኢያሪኮ ተነሣ፤ በመንገድ ሳለ ከከተማይቱ በርከት ያሉ ልጆች ወጥተው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ “አንተ ራሰ መላጣ ከዚህ ውጣ!” እያሉ ጮኹበት። ኤልሳዕም መለስ ብሎ ዙሪያውን በመቃኘት፥ አተኲሮ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ በዚህም ጊዜ ሁለት እንስት ድቦች ከጫካ ወጥተው ከእነዚያ ልጆች መካከል አርባ ሁለቱን ሰባብረው ጣሉአቸው። ኤልሳዕም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ ዘግየት ብሎ ግን ወደ ሰማርያ ተመለሰ።