ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 16
16
የይሁዳ ንጉሥ አካዝ
(2ዜ.መ. 28፥1-27)
1የረማልያ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ኻያ ዓመት ነበር፤ እርሱም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እርሱም የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት አልተከተለም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ አምላኩን እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ሥራ ሠራ፤ 3የእስራኤልንም ነገሥታት መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ የገዛ ልጁን እንኳ ሳይቀር ለጣዖቶች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ይህንንም የፈጸመው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ አገር ለመግባት ወደፊት እየገፉ በመጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚያች ምድር ነቃቅሎ ያስወገዳቸው አሕዛብ ይሠሩት የነበረውን አጸያፊ ድርጊት በመከተል ነው። #ዘዳ. 12፥31። 4አካዝ በየኰረብቶች ላይ በተሠሩት የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችና በእያንዳንዱም ዛፍ ሥር መሥዋዕት በማቅረብ ዕጣን አጠነ።
5የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል ከበቡአት፤ ነገር ግን አካዝን ድል ሊያደርጉት አልቻሉም። #ኢሳ. 7፥1። 6በዚያኑ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ረጺን የኤላትን ከተማ አስመልሶ በቊጥጥሩ ሥር በማድረግ በዚያ የነበሩትን አይሁድ አስወጣ፤ ያን ጊዜ በኤላት የሰፈሩት ኤዶማውያን እስከ አሁን በዚያ ይገኛሉ። 7ከዚህም የተነሣ ንጉሥ አካዝ ወደ አሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ቲግላት ፐሌሴር “እኔ ለአንተ ታማኝ አገልጋይህ ነኝ፤ ስለዚህም ወደ እኔ መጥተህ አደጋ ከጣሉብኝ ከሶርያና ከእስራኤል ነገሥታት እጅ አድነኝ” የሚል ጥያቄ የያዙ መልእክተኞች ላከ። 8ከዚህም በቀር አካዝ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት ሰብስቦ ለዚሁ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት በማድረግ ላከለት። 9የአካዝን ጥያቄ በመቀበል ቲግላት ፐሌሴር ዘምቶ ደማስቆን በቊጥጥሩ ሥር አደረገ፤ ንጉሥ ረጺንንም ገደለ፤ ሕዝቡንም ማርኮ ቂር ተብላ ወደምትጠራው ስፍራ ወሰደው።
10ንጉሥ አካዝ ወደ ደማስቆ ሄዶ ከንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር ጋር በተገናኘ ጊዜ በዚያ አንድ መሠዊያ አየ፤ ያንን መሠዊያ በተመሳሳይ ሁኔታ መሥራት የሚያስችለውን ቅርጽ አዘጋጅቶ ለካህኑ ለኡሪያ ላከለት፤ 11ስለዚህም ኡሪያ ንጉሥ አካዝ ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ልክ ያንኑ የሚመስል መሠዊያ ሠራ፤ 12አካዝም ከደማስቆ በተመለሰ ጊዜ ያ መሠዊያ በትክክል መሠራቱን ለማየትና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ፤ 13እንዲሁም በዚያ መሠዊያ ላይ የሚቃጠል የእንስሶች መሥዋዕትና የእህል መባ አቀረበ፤ የመባውን ወይን ጠጅና የኅብረት መሥዋዕት ደም አፈሰሰበት። 14ከነሐስ ተሠርቶ ለእግዚአብሔር የተለየውም መሠዊያ በዚያ አዲስ መሠዊያና በቤተ መቅደሱ መካከል ነበር፤ አካዝም ያንን መሠዊያ አስነሥቶ እርሱ ባሠራው በአዲሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን በኩል አኖረው፤ #ዘፀ. 27፥1-2፤ 2ዜ.መ. 4፥1። 15ከዚህ በኋላ ኡሪያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ይህን የእኔን ታላቅ መሠዊያ ማለዳ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ በምሽት ለሚቀርበውም የእህል መባ ስለ ንጉሡና ስለ ሕዝቡ የሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል መባ የሚቀርብበትና የሕዝቡ የወይን ጠጅ መባ የሚፈስበት እንዲሆን አድርግ፤ የሚሠዉትንም የእንስሶች ደም ሁሉ በእርሱ ላይ አፍስስ፤ ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ግን እኔ ራሴ የምፈልገውን ነገር የምጠይቅበት እንዲሆን አድርግ።” 16ኡሪያም ንጉሡ እንዳዘዘው አደረገ።
17ንጉሥ አካዝ በቤተ መቅደስ ውስጥ መገልገያ የነበሩትን ከነሐስ የተሠሩ መንኰራኲሮች ቈርጦ ልሙጥ የሆነውን ነገር ከጐናቸው ወሰደ። በእነርሱ ላይ የነበሩትንም የመታጠቢያ ሳሕኖች ወሰደ፤ ከነሐስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ከታች በኩል ተሸክመውት ከነበሩት ከነሐስ ከተሠሩት ከዐሥራ ሁለት የበሬ ቅርጾች ጀርባ ላይ አንሥቶ፥ ከድንጋይ በተሠራ መሠረት ላይ አኖረው። #1ነገ. 7፥23-39፤ 2ዜ.መ. 4፥2-6። 18አካዝ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለማስደሰት ሲል ንጉሣዊ ዙፋን የሚዘረጋበትን ሉዓላዊ ስፍራ አስወገደ፤ ከዚያ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ወደ ቤተ መቅደስ ይገባበት የነበረውንም ልዩ በር ዘጋ።
19ንጉሥ አካዝ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 20አካዝ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ። #ኢሳ. 14፥28።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 16: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997