ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:27-38

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:27-38 አማ05

ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳ ሁለተኛው ዓመት የረማልያ ልጅ ፈቁሔ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ኻያ ዓመት ገዛ። እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነትን በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ። የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር ዒዮን፥ አቤልቤትማዕካ፥ ያኖሐ፥ ቄዴሽና ሐጾር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች፥ እንዲሁም የገለዓድን፥ የገሊላንና የንፍታሌምን ግዛቶች በመውረር ሕዝቡን ወደ አሦር ማርኮ የወሰደውም ይኸው ፋቁሔ በነገሠበት ዘመን ነበር። የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠ በሃያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በንጉሥ ፋቁሔ ላይ ሤራ ጠነሰሰ፤ እርሱንም ገድሎ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ፈቁሔ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። የረማልያ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሩሻ ተብላ የምትጠራ የጻዶቅ ልጅ ነበረች። የአባቱንም የዖዝያን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብ መሠዊያዎችን አላስወገደም፤ ሕዝቡም መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ ቅጽር በር ያሠራ ይኸው ኢዮአታም ነበር። ኢዮአታም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሶርያ ንጉሥ ረጺንና፥ የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በይሁዳ ላይ አደጋ እንዲጥሉባት የላካቸው ይኸው ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠበት ዘመን ነበር፤ ኢዮአታም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝ ነገሠ።