ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 15
15
የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያ
(2ዜ.መ. 26፥1-23)
1ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት የአሜስያስ ልጅ ዖዝያ በይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኀምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። 3እርሱም የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ 4ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብን የማምለኪያ ቦታዎች አልደመሰሰም፤ ስለዚህም ሕዝቡ በየኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ 5በኋላም እግዚአብሔር በዖዝያ ላይ የቆዳ በሽታ አሳደረበት፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይህ በሽታ ስላልለቀቀው ከሥራው ሁሉ ተገልሎ በተለየ ቤት ውስጥ ለብቻው ይኖር ነበር፤ በዚህም ጊዜ መንግሥቱን ሲመራ የቈየው ልጁ ኢዮአታም ነበር።
6ንጉሥ ዖዝያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። 7ዖዝያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በቀድሞ አባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ። #ኢሳ. 6፥1።
የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ
8ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ስድስት ወር ገዛ፤ 9እርሱም ከእርሱ በፊት እንደ ነበሩት ነገሥታት ሁሉ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እንዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ 10ሻሉም ተብሎ የሚጠራው የያቤሽ ልጅ ሤራ በማድረግ ዪብለዓም ተብላ በምትጠራው ስፍራ ንጉሥ ዘካርያስን ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ።
11ንጉሥ ዘካርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።
12በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር ለንጉሥ ኢዩ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ በእስራኤል ይነግሣሉ” ሲል የተናገረው የተስፋ ቃል ተፈጸመ። #2ነገ. 10፥30።
የእስራኤል ንጉሥ ሻሉም
13ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የያቤሽ ልጅ ሻሉም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ አንድ ወር ብቻ ገዛ።
14ምናሔም ተብሎ የሚጠራው የጋዲ ልጅ ከቲርጻ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ሻሉምንም ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ። 15ሻሉም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ እንዲሁም እርሱ የጠነሰሰው ሤራ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 16ምናሔም ከቲርጻ ተነሥቶ በሚያልፍበት ጊዜ እግረ መንገዱን የቲፍሳሕን ከተማ፥ ነዋሪዎችዋንና በዙሪያዋ የነበረውን ግዛት ሁሉ ደመሰሰ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለእርሱ እጃቸውን ለመስጠት ባለመፍቀዳቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ነፍሰ ጡሮችን እንኳ ሳይምር ሆዳቸውን ቀደደ።
የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም
17ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ ዐሥር ዓመት ገዛ። 18እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱም እግዚአብሔርን አሳዘነ። 19የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር እስራኤልን ወረረ፤ ምናሔም በአገሩ መንግሥት ላይ ሥልጣኑን እንዲያጸናለትና እንዲደግፈው ለመማጠን ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር እጅ መንሻ አድርጎ ለቲግላት ፐሌሴር ሰጠው። 20ምናሔም ገንዘቡን የሰበሰበው የእስራኤል ከበርቴዎች እያንዳንዳቸው ኀምሳ ጥሬ ብር አዋጥተው እንዲሰጡ በማስገደድ ነበር። በዚህም ዐይነት ቲግላት ፐሌሴር በሰላም ወደ አገሩ ተመልሶ ሄደ።
21ምናሔም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 22ምናሔም ሞተ፤ ተቀበረም፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ፈቃሕያ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ፈቃሕያ
23ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፈቃሕያ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ 24እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 25ከፈቃሕያ ሠራዊት መካከል ፈቁሔ ተብሎ የሚጠራ የረማልያ ልጅ የሆነ አንድ የጦር መኰንን ከኀምሳ የገለዓድ ሰዎች ጋር ሆኖ ሤራ ጠነሰሰ፤ በሰማርያ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ዘልቆ በመግባትም ፈቃሕያን ከአርጎብና ከሃርዬ ጋር ገድሎ በፈቃሕያ እግር ተተክቶ ነገሠ።
26ፈቃሕያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።
የእስራኤል ንጉሥ ፈቁሔ
27ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳ ሁለተኛው ዓመት የረማልያ ልጅ ፈቁሔ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ኻያ ዓመት ገዛ። 28እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነትን በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ።
29የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር ዒዮን፥ አቤልቤትማዕካ፥ ያኖሐ፥ ቄዴሽና ሐጾር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች፥ እንዲሁም የገለዓድን፥ የገሊላንና የንፍታሌምን ግዛቶች በመውረር ሕዝቡን ወደ አሦር ማርኮ የወሰደውም ይኸው ፋቁሔ በነገሠበት ዘመን ነበር።
30የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠ በሃያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በንጉሥ ፋቁሔ ላይ ሤራ ጠነሰሰ፤ እርሱንም ገድሎ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ 31ፈቁሔ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታም
(2ዜ.መ. 27፥1-9)
32የረማልያ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 33በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሩሻ ተብላ የምትጠራ የጻዶቅ ልጅ ነበረች። 34የአባቱንም የዖዝያን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ 35ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብ መሠዊያዎችን አላስወገደም፤ ሕዝቡም መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ ቅጽር በር ያሠራ ይኸው ኢዮአታም ነበር።
36ኢዮአታም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 37እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሶርያ ንጉሥ ረጺንና፥ የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በይሁዳ ላይ አደጋ እንዲጥሉባት የላካቸው ይኸው ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠበት ዘመን ነበር፤ 38ኢዮአታም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 15: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997