ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 1
1
ነቢዩ ኤልያስና ንጉሥ አካዝያስ
1የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞአብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ።
2በዚህም ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ በሰማርያ ቤተ መንግሥቱ ሳለ ከሰገነቱ ላይ ወድቆ በብርቱ ስለ ቈሰለ ታሞ ነበር፤ እርሱም “እኔ ከዚህ ሕመም እድን ወይም አልድን እንደ ሆነ በፍልስጥኤም የዔክሮን ከተማ አምላክ የሆነውን ብዔልዜቡልን ጠይቃችሁልኝ ኑ” ብሎ መልእክተኞቹን ላከ። 3ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት፥ በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ በማሰብ ነውን?’ 4ስለዚህም እግዚአብሔር፥ ‘እነሆ አንተ ትሞታለህ እንጂ አትፈወስም! ከተኛህበት አልጋም አትነሣም! ብሎሃል’ በሉት።”
ስለዚህ ኤልያስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ 5መልእክተኞቹም ወደ ንጉሡ ተመልሰው ሄዱ፤ ንጉሡም “ስለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
6እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንድ ሰው በመንገድ አግኝቶን ወደ አንተ ተመልሰን እንድንመጣና እግዚአብሔር ስለ አንተ የተናገረውን እንድናስረዳህ አዘዘን፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክህበት ምክንያት ምንድን ነው? በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብለህ በማሰብህ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከዚህ ሕመም አትፈወስም! ከተኛህበትም አልጋ አትነሣም!’ ”
7ንጉሡም “በመንገድ ያገኛችሁትና ይህን ቃል የነገራችሁ ያ ሰው እንዴት ያለ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
8እነርሱም “ጠጒራም ልብስ ለብሶ በወገቡ ዙሪያ የጠፍር ቀበቶ የታጠቀ ነው” ሲሉ መለሱለት። #1፥8 ጠጒራም ልብስ ለብሶ፦ ወይም ሰውየው ጠጒራም ነው። #ማቴ. 3፥4፤ ማር. 1፥6።
ንጉሡም “እርሱማ ኤልያስ ነው!” አለ።
9ከዚህም በኋላ ንጉሡ አንዱን የጦር መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሄዶ ኤልያስን ይዞ ያመጣለት ዘንድ አዘዘው፤ መኰንኑም ኤልያስን በአንድ ኰረብታ ላይ ተቀምጦ አገኘውና “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው።
10ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ በዚያም ጊዜ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ።
11ንጉሡም እንደገና ሌላውን መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ እርሱም ወደ ኤልያስ ወጥቶ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አሁኑኑ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል!” አለው።
12ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር እሳት መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ። #ሉቃ. 9፥34።
13ንጉሡም ለሦስተኛ ጊዜ ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሌላ መኰንን ላከ፤ ይህኛው መኰንን ግን ወደ ኰረብታው በመውጣት በኤልያስ ፊት በጒልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት ሰዎች ምሕረት አድርግልን! ሕይወታችንንም ከሞት አድን! 14ሌሎቹን ሁለት መኰንኖችና ተከታዮቻቸውን ሁሉ ከሰማይ የወረደ እሳት በልቶአቸዋል፤ ለእኔ ግን እባክህ ምሕረት አድርግልኝ!”
15በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ኤልያስን “ከእርሱ ጋር አብረህ ውረድ፤ ከቶም አትፍራ” አለው። ስለዚህም ኤልያስ ከመኰንኑ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ፤ 16“እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘በእስራኤል አምላክ እንደሌለ በመቊጠር፥ የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን እንዲጠይቁልህ መልእክተኞች በመላክህ ምክንያት ትሞታለህ እንጂ አትድንም!’ ” አለው።
17እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በተናገረውም ቃል መሠረት አካዝያስ ሞተ፤ አካዝያስ ወንዶች ልጆች ስላልነበሩት በእርሱ እግር ተተክቶ ወንድሙ ኢዮራም ነገሠ፤ ይህም የሆነው የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ነበር።
18ንጉሥ አካዝያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997