የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11:1-15

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11:1-15 አማ05

ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እባካችሁ ታገሡኝ። እንደ አንዲት ንጽሕት ልጃገረድ በድንግልናዋ ለአንድ ባል እንደምትታጭ እኔም እናንተን ለክርስቶስ ስላአጨኋችሁ ስለ እናንተ መንፈሳዊ ቅናት እቀናለሁ። እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ሐሳብ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ያላችሁን ቅንና ንጹሕ የሆነ ታማኝነት ትተዋላችሁ ብዬ እፈራለሁ። አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ የሰበክነውን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም እናንተ የተቀበላችሁትን መንፈስ ሳይሆን ሌላ መንፈስ ብትቀበሉ፥ ወይም የተቀበላችሁትን ወንጌል ሳይሆን ሌላ ወንጌል ብትቀበሉ፥ ዝም ብላችሁ ተሸነፋችሁ ማለት ነው። ነገር ግን እኔ ከነዚህ ታላላቅ ሐዋርያት በምንም ነገር የማንስ አይመስለኝም። በአነጋገር ፈሊጥ ምሁር ባልሆንም እንኳ ዕውቀት አይጐድለኝም፤ ይህንንም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ በግልጥ አስረድተናችኋል። እኔ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ለእናንተ መስበኬና እናንተን ከፍ ለማድረግ ራሴን ማዋረዴ ምናልባት እንደ ኃጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን? እናንተን ለማገልገል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያን ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ። ከእናንተ ጋር ሳለሁ ችግር በደረሰብኝ ጊዜ ከመቄዶንያ የመጡ ወንድሞች በሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ይረዱኝ ስለ ነበር በማንም ሸክም አልሆንኩም፤ እስከ አሁን በእናንተ ላይ በምንም ነገር ሸክም አልሆንኩም፤ ለወደፊትም ሸክም አልሆንባችሁም። የክርስቶስ እውነት በእኔ ውስጥ በመኖሩ እንዳልመካ የሚያደርገኝ በአካይያ አገሮች ማንም የለም። ምክንያቱስ ምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነውን? እንደምወዳችሁስ እግዚአብሔር ያውቃል። እነዚያ ሌሎች ሐዋርያት “እኛም እንደ እነርሱ እንሠራለን” እያሉ የሚመኩበትን ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደፊትም ደግሞ አደርጋለሁ። እንደእነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው። ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ሰይጣን እንኳ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለውጣል። ስለዚህ እነዚህ የሰይጣን አገልጋዮች የጽድቅ አገልጋዮችን ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ አያስደንቅም፤ በመጨረሻ የሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ።