በዚህም ዐይነት ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት፥ የፋሲካ በዓል አከባበርና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ የማቅረቡ ሥራ ሁሉ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በዚያ ቀን ተከናወነ። በዚያ የነበሩ እስራኤላውያን ሁሉ የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ እንዲሁም ለሰባት ቀን የቂጣን በዓል አከበሩ፤ ከነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ጀምሮ የፋሲካ በዓል ይህን በመሰለ ሁኔታ ከቶ ተከብሮ አያውቅም፤ ንጉሥ ኢዮስያስ፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ የይሁዳ፥ የእስራኤልና የኢየሩሳሌም ሕዝብ የፋሲካን በዓል አሁን ባከበሩት ዐይነት ከዚህ በፊት ከነበሩት ነገሥታት መካከል፥ አንዱ እንኳ አክብሮ አያውቅም፤ ይህም በዓል የተከበረው፥ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ነበር። ንጉሥ ኢዮስያስ ለቤተ መቅደሱ ይህን ሁሉ ካደራጀ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው ካርከሚሽ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ አደጋ ለመጣል ሠራዊቱን አሰልፎ መጣ፤ ኢዮስያስም ሊቋቋመው ተነሣ፤ ኒካዑ ግን ለኢዮስያስ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ እኔንና አንተን የሚያጣላን ምንም ነገር የለም፤ እኔ የመጣሁት ጠላቶቼን ለመውጋት እንጂ፥ አንተን ለመውጋት አይደለም፤ ጠላቶቼንም በፍጥነት እንድወጋ እግዚአብሔር አዞኛል፤ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ስለ ሆነ፥ ባትቃወመኝ ይሻልሃል፤ እምቢ ብትል ግን እግዚአብሔር ያጠፋሃል” የሚል መልእክት ላከበት፤ ኢዮስያስ ግን ጦርነት ለመግጠም ቊርጥ ውሳኔ አደረገ፤ እግዚአብሔር በንጉሥ ኒካዑ አማካይነት የተናገረውንም ሊሰማ አልፈለገም፤ ልብሰ መንግሥቱን ለውጦ ሌላ ሰው በመምሰል በመጊዶ ወደሚገኘው ሜዳ ሊዋጋ ሄደ። ጦርነቱም በመፋፋም ላይ ሳለ፥ ንጉሥ ኢዮስያስ ከግብጽ ወታደሮች በተወረወረ ቀስት ተወጋ፤ እርሱም አገልጋዮቹን፥ “ክፉኛ ቈስያለሁና ከጦር ሜዳው አውጡኝ!” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ከሠረገላው አውጥተው እዚያ በነበረው በሌላ ሠረገላ ውስጥ በማስቀመጥ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዚያም ሞተ፤ በነገሥታትም መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች ሁሉ አለቀሱለት። ነቢዩ ኤርምያስም ለንጉሥ ኢዮስያስ የለቅሶ ሙሾ አወጣለት፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች አልቃሾች ኢዮስያስን በማስታወስ፥ በሚያለቅሱበት ጊዜ በዚሁ በነቢዩ ኤርምያስ የለቅሶ ሙሾ ማልቀስ በእስራኤል አገር የተለመደ ሆነ፤ ይህም የለቅሶ ሙሾ የእስራኤልን የለቅሶ ሰቆቃ በያዘ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር የነበረው ታላቅ ፍቅር፥ ለእግዚአብሔር ሕግ የነበረው ታዛዥነት፥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለው የእርሱ ታሪክ ጭምር በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:16-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች